AMN-ሚያዚያ 27/2018 ዓ.ም
በመጋቢት ወር በአዲስ አበባ በተካሄደው “ኢንቨስት ኢይ ኢትዮጵያ 2026” የመድረክ ስነ-ስርዓት ላይ ቻይናዊያን ኩባንያዎች 10.5 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጡ የኢንቨስትመንት ስምምነቶችን በመፈራረም ቀዳሚ መሆናቸውን ቻይና ዴይሊ የተሰኘው ጋዜጣ በዛሬ ዕትሙ ይዞት በወጣው ፅሁፍ በስፋት አትቷል።
ስምምነቶቹ ከአሞኒያ ምርት እስከ ኤሌክትሪክ መሳሪያዎች ማምረቻ ድረስ የሚሸፍኑ ሲሆን፣ ይህ ደግሞ በኢትዮጵያ በተለይም በታዳሽ ኃይል፣ በማኑፋክቸሪንግ እና በከባድ ኢንዱስትሪ ዘርፎች የቻይና ኢንቨስትመንት እያደገ መምጣቱን ያሳያል።
በኢትዮጵያ ሙዋለ ነዋያቸውን ኢንቨስት ለማድረግ ፍላጎት ካሳዩ ከዐሥራ ሁለት በላይ ከሚሆኑ ታዋቂ ኩባንያዎች መካከል፣ ሁለት የቻይና ኩባንያዎችን ጨምሮ ሰባቱ በድምሩ 13.1 ቢሊዮን ዶላር ኢንቨስት ያደርጋሉ። ይህ ኢንቨስትመንት የሥራ ዕድልን ከመፍጠር አንፃር፣ ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶችን እንደሚያሳድግ እና በውጭ ምርቶች ላይ ያለን ጥገኛነት እንደሚቀንስ ይጠበቃል ሲልም ጋዜጣው አስነብቧል።
የኢትዮጵያ እና የቻይና የኢንቨስትመንት ትብብር በሁለት ዋና ዋና መንገዶች ሊታይ ይችላል።
የመጀመሪያው የኢትዮጵያን የወጪ ንግድ አቅም የሚያሳድጉ ዘርፎች ላይ የሚደረግ ቀጥተኛ የገንዘብ ኢንቨስትመንት ነው። የሁዋጂያን ግሩፕ (Huajian Group) በኢስተርን ኢንዱስትሪ ፓርክ የጫማ ማምረቻ ፋብሪካ ለሺዎች ስራ እድል የፈጠረ ሲሆን፣ በየቀኑ ወደ 15,000 ጥንድ ጫማዎችን ያመርታል።
ሁለተኛው የቻይና ኢንቨስትመንቶችን የሚደግፍ ወሳኝ መሠረተ ልማት የመገንባት ሚና ነው። ከኢትዮጵያ-ጅቡቲ የባቡር መስመር ጀምሮ እስከ ኢንዱስትሪ ፓርኮች እና ልዩ የኢኮኖሚ ቀጠናዎች ድረስ ቻይና የምታደርገው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን የጠቀሰው ዘገባው እ.ኤ.አ በ2018 የተመረቀው 752 ኪሎ ሜትር የባቡር መስመር ከ12 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን በላይ ጭነት ያጓጓዘ ሲሆን፣ የሎጂስቲክስ ወጪን በ30 በመቶ መቀነሱን ጠቅሷል።