የገላን ጉራ ኢንዱስትሪ ፓርክ የምርታማነት አቅም ህልማችንን የምናሳካበት ምቹና ዘመናዊ የሥራ ከባቢ ነው

You are currently viewing የገላን ጉራ ኢንዱስትሪ ፓርክ የምርታማነት አቅም ህልማችንን የምናሳካበት ምቹና ዘመናዊ የሥራ ከባቢ ነው

AMN- ግንቦት 8/2018 ዓ.ም

የገላን ጉራ ኢንዱስትሪ ፓርክ የምርታማነት አቅም ህልማቸውን የሚያሳኩበት ምቹና ዘመናዊ የሥራ ከባቢ መሆኑን በፓርኩ ማምረት የጀመሩ አምራቾች ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለመካከለኛና ከፍተኛ አምራች ኢንዱስትሪዎች ትልቅ ተስፋ የሰነቀውንና በሺዎች ለሚቆጠሩ ወጣቶች የሥራ ዕድል የሚፈጥረውን የገላን ጉራ ኢንዱስትሪ ፓርክ በይፋ መርቀው ከፍተዋል።

በፓርኩ ውስጥ ማምረት የጀመሩ አምራቾች እንደገለጹት፤ በተሰናሰለ የኢንዱስትሪ ማምረቻ ስፍራ የተገነባው የገላን ጉራ ኢንዱስትሪ ፓርክ የመስሪያ ቦታ ችግራቸውን የቀረፈ መሆኑን ተናግረዋል።

የገላን ጉራ ምቹ የማምረቻ ኢንዱስትሪ ምኅዳር ምርታማነትን በተሻለ አቅም በመገንባት ከፍተኛ ተነሳሽነትን የሚፈጥር እንደሆነ ገልጸዋል።

የአማሄ ማኑፋክቸሪንግ ሥራ አስኪያጅ ዮኃንስ አየለ እንደሚሉት፤ የገላን ጉራ ኢንዱስትሪ ፓርክ ዘመናዊ መሰረተ ልማት የተሟላለትና ደረጃቸውን የጠበቁ ምርቶችን ማምረት የሚያስችል ነው።

ፓርኩ የነበረባቸውን የመስሪያ ቦታ ችግር በመቅረፍ ጥራትና ደረጃቸውን የጠበቁ ምርቶችን በተሻለ ጥራት በማምረት የገበያ ተወዳዳሪነትን ለማጎልበት ዘርፈ ብዙ ፋይዳ ያለው መሆኑን ተናግረዋል።

የአማሄ ማኑፋክቸሪንግም ኃይል ቆጣቢና ከብክለት የፀዱ የኤሌክትሪክ ምድጃ፣ ምጣድና ሌሎች ምርቶችን የማምረት አቅም ለማጎልበት ከፍተኛ መነሳሳት የሚፈጥር ወርቃማ ዕድል ነው ብለዋል።

ፓርኩ የምርታማነት አቅም ህልማችንን ዕውን የምናደርግበት ምቹ የሥራ ከባቢ ነው ሲሉም ገልጸዋል።

የታሬ ነጋ ጄኔራል ትሬዲንግ ተወካይ እሱባለው ዋሌ በበኩላቸው፤ የገላን ጉራ ኢንዱስትሪ ፓርክ ዘመናዊ መሠረተ ልማትን ከውጤታማ ቴክኖሎጂ አሰናስሎ የተገነባ አስደናቂ ፕሮጀክት ነው ብለዋል።

በዚህ የኢንዱስትሪ ፓርክ የማምረት ዕድል ማግኘታቸው ጥራትና ደረጃቸውን የጠበቁ የቤትና የቢሮ መገልገያ ምርቶችን በተሻለ አቅም ለማምረት መነሳሳት የሚፈጥር መሆኑን ገልጸዋል።

የሜጋ ፈርኒቸር ተወካይ ዮኃንስ እንድሪያስ፤ ከዚህ ቀደም የኃይል መቆራረጥ፣ የመስሪያ ቦታ አለመመቻቸትና የመሠረተ ልማት ክፍተት በምርታማነታቸው ላይ ጫና ሲያሳድር መቆየቱን ተናግረዋል።

የገላን ጉራ ኢንዱስትሪ ፓርክ ዘመናዊ የቤትና የቢሮ መገልገያ ምርቶችን የማምረት አቅሙን በማላቅ ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር ያስቻለ ምቹ የሥራ ምኅዳር መፍጠሩን መጠቆማቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review