AMN-ግንቦት 11/2018 ዓ.ም
ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ሰላማዊ ፣ ነጻ ፣ ፍትሃዊና ዲሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅና የፖለቲካ ፓርቲዎች በምርጫው ሂደት ሊኖራቸው በሚገባው ሚና ዙሪያ የአዲስ አበባ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰፊ ውይይት አካሄደ።
በውይይቱ ላይ የፓርቲዎች ሚና፣ የፖለቲካ ምህዳሩን ማስፋት እንዲሁም የምርጫን ውጤት በጸጋ የመቀበል ባህልን ማዳበር በሚቻልባቸው አቅጣጫዎች ላይ ሰፊ ምክክር ተደርጓል።
የጋራ ምክር ቤቱ ሰብሳቢ አቶ ማሩ ጃኔ ለኤ ኤም ኤን እንደገለጹት ፣ ምርጫው በሰላም እንዲጠናቀቅ የፓርቲዎችና የምክር ቤቱ ሚና ምን መሆን አለበት በሚለው ላይ ትኩረት ተደርጎ ተወያይተዋል፡፡
ማንም ያሸንፍ ማንም፣ አንደኛ ምርጫውን በሰላማዊ መንገድ እንዲጠናቀቅ መስራት፤ ሁለተኛ ደግሞ የመጣውን ውጤት በጸጋ ተቀብሎ ችግሮች ቢኖሩ እንኳን በሰለጠነ ፖለቲካዊ አግባብ መፍታት እንሚገባ ነው አቶ ማሩ ጃኔ የገለጹት፡፡

ገዢው ፓርቲም የምክር ቤቱ አባል በመሆኑ እንደ መንግስትና እንደ ፓርቲ የሚነሱ ጥያቄዎችንና ችግሮችን በጋራ እየገመገሙ ለመፍታት ጥረት ሲደረግ መቆየቱን የገለጹት አቶ ማሩ፤ መንግስትም የምርጫውን ምህዳር በማስፋትና ለፓርቲዎች ምቹ ሁኔታን በመፍጠር ረገድ ጥሩ ስራዎችን እየሰራ እንደሚገኝ አክለዋል።
የህብር ኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ ምክትል ሊቀመንበር አቶ አበራ በቀለ በበኩላቸው፣ እስካሁን የተሰሩት ስራዎች ሰላምን፣ የሀገርን የጋራ ጉዳዮችና አንድነትን ባከበረ መልኩ መከናወናቸውን አውስተዋል።
አቶ አበራ አክለውም፣ የሃሳብ የበላይነት ያለው ፓርቲ አሸንፎ ስልጣን ቢይዝ ያንን ሁኔታ በጸጋ ለመቀበል፣ ካሸነፍን መንግስት ሆነን ሀገር የምንመራበትን የጋራ መስመር ለማስመር፣ ከተሸነፍንም ደግሞ ላሸነፈው አካል በምስጋና የምናስተላልፍበትን አቅጣጫ ያስቀመጠ ጥሩ ውይይት ነበር ብለዋል።
የአዲስ አበባ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት የወጣቶች ክንፍ ሰባሳቢ አቶ ዳግላስ ወልደ ስላሴ፤ በዚህች ሀገር ላይ መንግስት መሆን የሚቻለው በምርጫ ብቻ እንደሆነና ከዚህ የተሻለ መንገድ እንደሌለ ፓርቲዎች እንደሚያምኑ ገልጸው፣ ፓርቲዎች አማራጭ ፖሊሲና ሃሳቦቻቸውን ለህዝብ አቅርበው በሚመረጡበት በዚህ ሂደት ላይ በንቃት መሳተፍ እንደሚገባ አሳስበዋል።

የወሎ ሕዝብ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ ተወካይ አቶ መሃመድ ቦሩ ፣ ፓርቲዎች አማራጭ ሃሳቦቻቸውን በተለያዩ ሚድያዎች ሲያቀርቡ መቆየታቸውንና ህዝቡም ይህንን አይቶ የሚፈልገውን ፓርቲ እንደሚመርጥ እንደሚጠብቁ ተናግረዋል።
የጋራ ምክር ቤቱ የዲሞክራሲ ባህል እንዲያብብ አደራጃጀቱን ጠብቆ ሃሳቡን ወደ ህዝብ እንዲያደርስና የሚዲያ ተደራሽነት እንዲኖረው በማመቻቸት ረገድ ከፍተኛ ድጋፍ ላበረከቱት በብልፅግና ፓርቲ የአዲስ አበባ ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት የዲሞክራሲ ባህል ግንባታ ዘርፍ ሀላፊ ለዶክተር መዕሳ ኤሊማ እውቅና ሰጥቷል።
በፍሬሕይወት ብርሃኑ