AMN- ግንቦት 12/2018 ዓ.ም
እንደ ምርጫ ባሉ ወሳኝ ሀገራዊ ሂደቶች የመገናኛ ብዙኃን ሚና እጅግ የላቀ መሆኑን የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር እናትዓለም መለሰ ገለጹ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እና የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን “ለዲሞክራሲያዊ ምርጫ ስኬት የመገናኛ ብዙሃን ሚና” በሚል ርዕስ በጋራ ያዘጋጁት መድረክ በአዳማ ከተማ እየተካሄደ ነው።
መድረኩ ዴሞክራሲያዊ እና ፍትሃዊ ምርጫ ማካሄድ የሁሉም ባለድርሻ አካላት የጋራ ኃላፊነት መሆኑን ለማስገንዘብ ታስቦ የተዘጋጀ ነው።
በመድረኩ የተገኙት የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር እናትዓለም መለሰ በመድረኩ ባደረጉት ንግግር እንደ ምርጫ ባሉ ወሳኝ ሀገራዊ ሂደቶች የመገናኛ ብዙኃን ሚና እጅግ የላቀ ነው ብለዋል።

መገናኛ ብዙሃን ብሔራዊ መግባባት በመፍጠር፣ የዜጎችን የፖለቲካ ንቃት በማጎልበትና ተጠያቂነት የሰፈነበት ስርዓት እንዲፈጠር በማድረግ በኩል ትልቅ አቅም አላቸው ነው ያሉት።
እንዲሁም በሀገር ግንባታ፣ ሕዝብን በማሳወቅና ለተግባር ለማነሳሳት የማይተካ ሚና እንዳላቸው ጠቁመው በተለይም እንደ ምርጫ ባሉ ወሳኝ ሀገራዊ ሂደቶች የመገናኛ ብዙኃን ሚና እጅግ የላቀ እንደሆነ ገልጸዋል።
የምርጫ ሂደቱን ግልጽነት እና ተጠያቂነት ባለው መልኩ በመከታተልና በመዘገብ፣ ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊ፣ አሳታፊና ተአማኒ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ኃላፊነታቸውን መወጣት እንዳለባቸውም ተናግረዋል። በቀሪ የምርጫ ቀናትም ይህንኑ ስራቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ አሳስበዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዋና ስራ አስፈጻሚ ሰይፈ ደርቤ በበኩቸው በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ብረተሰቡን ዝግጁ በማድረግ በኩል በርካታ ስራዎች ሲሰራ መቆየቱን ተናግረዋል። ይህ መድረክም የዛ አካል መሆኑን ጠቁመው አጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት።

በመድረኩ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር እናትዓለም መለሰ፣ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ተስፋሁን ጎበዛይ፣ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዋና ስራ አስፈጻሚ ሰይፈ ደርቤ፣ የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ፋሲካው ሞላ፣ የመገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን የስራ ሃላፊዎች፣ የመገናኛ ብዙሃን የስራ ሀላፊዎች እና ጋዜጠኞች መታደማቸውን ኢዜአ ዘግቧል።