AMN- ግንቦት 14/2018 ዓ.ም
በአዲስ አበባ የመንግስት ቋሚ ንብረቶች በዘመናዊ የንብረት መረጃ ሥርዓት በመመዝገቡ የመንግስት ሃብትና ንብረት እንዳይባክን ማስቻሉን የአዲስ አበባ ከተማ የመንግስት የንብረት አስተዳደር ባለስልጣን ገለጸ፡፡
በቢሮ ሃላፊ ደረጃ የአዲስ አበባ ከተማ የመንግስት የንብረት አስተዳደር ባለስልጣን የህንጻ ዘርፍ ምክትል ስራ አስኪያጅ አቶ ጥላሁን ከበደ ለኤ ኤም ኤን እንዳሉት ፣ በከተማዋ የመንግስት ሃብትና ንብረት በትክክል ተለይቶ እንዲታወቅ እየተደረገ ነው፡፡
ቢሮው ከአዲስ አበባ ከተማ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ቢሮ ጋር በመቀናጀት ዘመናዊ የሆነ የንብረት መረጃ ሥርዓት በመዘርጋት የመንግስት ቋሚ ንብረቶች እንዲመዘገቡ የማድረግ ሥራ እያከናወነ ይገኛል ብለዋል፡፡

እስካሁን ወደ 699 ያህል ተቋማት ቋሚ ንብረቶቻቸው ተመዝግበዋል ያሉት አቶ ጥላሁን ከበደ ፣ አጠቃላይ በተቋማትና በአመራር እንዲሁም በባለሙያዎች ምን ምን ንብረቶች እንዳሉ በትክክል ማወቅ የሚቻልበትና የንብረቶች ወቅታዊ ዋጋም በስርዓቱ መሰረት ተዘጋጅቶ ወደ ተግባር መግባቱን አንስተዋል፡፡
በማእከል፣ በክፍለ ከተማና በወረዳ ያሉ 6 ሺህ 945 ያህል የመንግስት ህንጻዎችን በዘመናዊው የንብረት መረጃ ሥርዓት እንዲመዘገቡ ተደርጓል ብለዋል፡፡
ይሄም ያለውን ሃብት በትክክል ቆጥሮ ለማወቅ እንዳስቻለ መሆኑንና ለፖሊሲና ህግ አውጭዎች እንዲሁም ከተማ አስተዳደሩን እየመሩ ላሉ አካላት የተሟላ መረጃ ለማቅረብ የሚያስችል ስርዓት መሆኑን አመላክተዋል፡፡
የሻምበል ምህረት