የከተማዋ ልማት አካታችነት እስከ ምን?

You are currently viewing የከተማዋ ልማት አካታችነት እስከ ምን?

አዲስ አበባ በፈጣንና ዘመናዊ የለውጥ ጉዞ ውስጥ ትገኛለች። ለረጅም ዓመታት በትራፊክ መጨናነቅና ክፍት በሆኑ አረንጓዴ ስፍራዎች እጥረት ስትታማ የኖረችው መዲናዋ፣ ዛሬ ግን በታላላቅ የኮሪደር ልማቶችና የወንዝ ዳርቻ ፕሮጀክቶች አማካኝነት ገጽታዋን እየቀየረች ነው። እነዚህ ልማቶች  ለከተማዋ አዲስ የህይወት ዘይቤ ከማላመዳቸውም በላይ፣ ነዋሪዎቿ ለዓመታት አጥተውት የነበረውን አረንጓዴ ስፍራና አማራጭ የመዝናኛ ስፍራዎች እንዲያገኙ አዲስ በር መክፈት ችለዋል፡፡

ይህ ሰፊና አካታች የመሰረተ ልማት ግንባታ ከተማዋን ወደ ላቀ የውበትና የፅዳት ደረጃ ከማሸጋገሩም ባሻገር፣ በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ሥነ-ልቦናዊ ዘርፎች ላይ የራሱን ትልቅ አሻራ ማሳረፍ ጀምሯል። በተለይ ለዘመናት የቆየውን የመዝናኛ ስፍራዎች እጥረት በከፍተኛ ደረጃ በመቅረፍ ረገድ የፈጠረው መነቃቃት በቀላሉ የሚገመት አይደለም። አዲስ ልሳን ጋዜጣም ባሳለፍነው ሐሙስ የተመረቀውን የኢኮ-ፓርክን ጨምሮ ሌሎች በከተማዋ የተሰሩት ታላላቅ የመዝናኛ ሥፍራዎች የነዋሪውን የአኗኗር ዘይቤ በመቀየር፣ የከተማዋን መልካም ገጽታ በመገንባትና የቱሪዝም ዘርፉን በማነቃቃት ረገድ ያላቸውን ሁለንተናዊ ፋይዳ በተመለከተ አጭር ዳሰሳ አድርጓል፡፡

አዲሶቹ የህዝብ መዝናኛ ፓርኮች ለመዲናዋ ምን አዲስ ነገር ይዘው መጡ?

የአዲስ አበባን የከተማነት ታሪክ በአዲስ ምዕራፍ እየጻፉ ያሉት መጠነ-ሰፊ የኮሪደር ልማቶችና ዘመናዊ ሜጋ ፕሮጀክቶች፣ መዲናዋን ወደ ላቀ የውበትና የኑሮ ምቹነት ደረጃ እያሸጋገሯት ይገኛሉ። ይህ ከተማዋን አረንጓዴ፣ ውብና ለነዋሪዎቿ ተስማሚ ለማድረግ የተወጠነው ዕቅድ፣ በአሁኑ ወቅት ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ በርካታ ታላላቅ ፓርኮችን ለህዝብ ማበርከት ችሏል። ይህ ግዙፍ እንቅስቃሴ የከተማዋን ገጽታ ከመቀየር ባለፈ፣ ነዋሪው ከቤት ውጭ የሚያሳልፈውን የመዝናኛ ባህል በማነቃቃትና አዲስ አበባን በአፍሪካ ቀዳሚ የከተማ ቱሪዝም መዳረሻ በማድረግ ረገድ የላቀ ሚና እየተጫወተ ይገኛል።

በመዲናዋ እየተመዘገበ ላለው አረንጓዴና ዘመናዊ የከተማ ዕድገት በተጨባጭ ማሳያ የሚሆነውና ባሳለፍነው ሳምንት ሐሙስ ዕለት በአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በይፋ የተመረቀው አዲሱ የኢኮ ፓርክ አንዱ ነው፡፡ ፓርኩ በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ልዩ ስሙ አስኮ አዲስ ሰፈር አካባቢ የተሰራ ሁለገብ የሕዝብ መዝናኛ ፓርክ ነው። ከንቲባ አዳነች አቤቤ በማህበራዊ የትስስር ገጻቸው የፓርኩን መመረቅ አስመልክተው ባጋሩት ጽሑፍ “ቦታው ከዚህ በፊት የቆሻሻ መጣያ የነበረ፣ ሕገ-ወጦችም ያለአግባብ ይጠቀሙበት የነበረ ሲሆን፣ ዛሬ በርካታ እሴቶች ተጨምረውበት መንፈስን የሚያድስ፣ ሕዝብ በጋራ የሚጠቀምበት ንፁህ አካባቢን ፈጥሯል” ብለዋል።

ይህ በላቀ ጥራትና ውበት የተገነባው የኢኮ ፓርክ በ30 ሺህ ካሬ ሜትር ሰፊ መሬት ላይ ያረፈ ሲሆን፣ ለአካባቢው ነዋሪዎችና ለከተማዋ ተለዋጭ የመዝናኛ አማራጮችን በስፋት የያዘ ነው። ፓርኩ ዘመናዊ ምህንድስናን ከተፈጥሮ ውበት ጋር አጣምሮ በውስጡ ማራኪ የውሃ ምንጭ (ፋውንቴን)፣ ደረጃውን የጠበቀ የእግር ኳስ ሜዳ፣ ደህንነቱ የተጠበቀ የህጻናት መጫወቻ ስፍራ፣ የባህልና ሥነ-ጥበብ ስራዎች ማቅረቢያ አምፊ-ቴአትር፣ እንዲሁም ዘመናዊ ካፌቴሪያ፣ ሱቆችና የጁስ ባርን አካቶ ይዟል። ከዚህ በተጨማሪ ለጎብኚዎች ምቾት ሲባል ሰፊ የመኪና ማቆሚያ (ፓርኪንግ)፣ ዘመናዊ የሻወርና የመፀዳጃ ክፍሎች እንዲሁም ረጃጅም የሰውነት ማጎልመሻና የእግር ጉዞ መሄጃ መንገዶች በጥራት ተሟልተውለታል።

ይህ ግዙፍና አካታች የኢኮ-ፓርክ ማህበራዊ ደረጃና የኑሮ ልዩነት ሳይገድበው ህጻናት፣ ወጣቶች፣ አረጋውያን እና አጠቃላይ የህብረተሰብ ክፍሎች ድሃ ሃብታም ሳይሉ በጋራ የሚገለገሉበት ጠንካራ የማህበራዊ ትስስር መድረክ ሆኖ የተሰራ ፕሮጀክት ነው። ከዚህ ፓርክ በተጨማሪ ከሳምንት በፊት የተመረቀው የአራዳ ፓርክም ብዙዎችን ያስደነቀ ሌላኛው ፕሮጀክት ሆኗል፡፡

የአራዳ ፓርክ በውስጡ የከተማዋን የስፖርትና የመንገድ መሰረተ ልማት ለማሳደግ እያንዳንዳቸው 5 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያላቸው የአስፓልት መንገድ፣ የብስክሌት መስመርና የመሮጫ መም እንዲሁም 6 ኪሎ ሜትር የሚረዝም ምቹ የእግረኛ መንገድ አካትቶ ይዟል። የአካባቢውን ጥንታዊ ለውጥ ይበልጥ ለማድመቅም በዙሪያው የነበሩ ከ700 በላይ ቤቶችና ሕንፃዎች ታሪካዊ ይዘታቸውን ሳይለቁ በጥንቃቄ እንዲታደሱ ተደርጓል።

ይህ ዘመናዊ ማዕከል ለንግድና ለፋይናንስ አገልግሎቶች ልዩ ትኩረት የሰጠ ሲሆን፣ ከፒያሳ ለተነሱ ነጋዴዎች ቅድሚያ የተሰጠባቸው 131 ዘመናዊ ሱቆች፣ 7 ካፌዎችና ሬስቶራንቶች፣ 1 ትልቅ ሱፐርማርኬት እና 1 የባንክ ቅርንጫፍ በውስጡ ይዟል። ከዚህ ባሻገርም ለአካል ብቃት እንቅስቃሴ የሚሆን 1 ዘመናዊ ጅምናዚየም፣ 7 አዳራሾች፣ ለተለያዩ ኩነቶች ማዘጋጃ የሚውሉ 8 ፕላዛዎች እና 3 አምፊ-ቲያትሮች የተገነቡለት ሲሆን፣ በሀገራችን ረጅሙ የሆነው ባለ 100 ሜትር የብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማ መስቀያ እና በአይነቱ ልዩ የሆነው “ዳንሲንግ ፋውንቴን” ለፓርኩ ልዩ ብሔራዊ ግርማ ሞገስ አላብሰውታል። ለቤተሰብና ለህጻናት ምቾት ሲባልም 4 ዘመናዊ የመጫወቻ ስፍራዎች፣ ህፃናት ስለ ሀገራቸው እውቀት የሚቀስሙበት “ትንሿ ከተማ”፣ 15 ሄክታር አረንጓዴ ተክሎች፣ 22 የሕዝብ መጸዳጃ ቤቶች የተገነቡ ሲሆን፣ በአንድ ጊዜ 131 መኪናዎችን መያዝ የሚችል የመኪና ማቆሚያም አለው፡፡ የአራዳ ፓርክ የታሪክ መመልከቻ ጋለሪን፣ ሆቴሎችን፣ የውበት ሳሎኖችን እና የግብይት ማዕከላትን በአንድ ጥላ ስር በማቀፍ የአዲስ አበባ አዲሱ የቱሪስት መዳረሻና መለያ ምልክት መሆን ችሏል።

ከዚህ በተጨማሪ በከተማዋ እምብርት ላይ የተሰሩት የአንድነት ፓርክ፣ የወዳጅነት አደባባይ እንዲሁም ተፈጥሮን ከዘመናዊነት ጋር ያቀላቀለው የእንጦጦ ተፈጥሮ ፓርክ በአሁኑ ወቅት የመዲናዋ አዳዲስ የኩራት መለያና ህያው ምስክሮች ሆነዋል። ከእነዚህ ታላላቅ ስራዎች ጎን ለጎን፣ በቅርቡ በተከናወኑ የኮሪደር ልማቶች አማካኝነት በታሪካዊቷ ፒያሳ፣ በፍልውሃ እና በአዋሬ ወንዝ ዳርቻዎች ላይ የተገነቡት አዳዲስ ክፍት የህዝብ መዝናኛዎች ለከተማዋ ተጨማሪ ማራኪ ውበትና የንጹህ አየር መተንፈሻ መሆን ችለዋል። እነዚህ አዳዲስ ስፍራዎች ከተማዋ ለዘመናት ተጭኗት ከነበረው የህንጻ ብዛት ውጥረት አውጥተው ወደ አረንጓዴ ስፍራነት ቀይረዋታል።

ይህ የመዝናኛ አማራጮችን የማስፋፋት ስራ በአዳዲስ ግንባታዎች ላይ ብቻ የተገደበ አይደለም፤ ይልቁንም በነዋሪዎቿ ልብ ውስጥ ትልቅ ቦታ ያላቸውን ቀደምት ታሪካዊ ስፍራዎችም ያካተተ ነው። በዚህ መሰረትም እንደ ብሔረ ፅጌ፣ ሐምሌ 19፣ አምባሳደር እና የጉለሌ እፅዋት ማዕከል ያሉ አንጋፋ የመዝናኛ ስፍራዎች የነበራቸውን ታሪካዊ ጠረን ሳይለቁ፣ በዘመናዊ መልክና በላቀ ውበት ታድሰው ለአገልግሎት ክፍት መደረጋቸው የከተማዋን ውበት በእጥፍ አሳድጎታል። ይህም አሮጌውንና አዲሱን ትውልድ በአረንጓዴ ስፍራዎች የሚያገናኝ ውብ ድልድይ ፈጥሯል።

የባህል፣ የሰላምና ኪነ-ጥበብ ተመራማሪው ወሰን ባዩ (ዶ/ር) በመዲናዋ እየተገነቡ ያሉ የመዝናኛ ሥፍራዎች፣ ቴአትርና ሲኒማ ቤቶች ትልቅ ሀገራዊ ፋይዳ እንዳላቸው ከዚህ ቀደም ለዝግጅት ክፍላችን በሰጡት አስተያየት ተናግረዋል፡፡ “የአንድ ሀገር ኪነ-ጥበባዊ ሥራዎች እንዲያድጉ ሲኒማ ቤቶችና የጥበብ መከወኛ ሥፍራዎች ቁልፍ ናቸው” ያሉት ተመራማሪው፣ የኪነ-ጥበብ ዕድገት ደግሞ በተዘዋዋሪ መንገድ የእሴት መጎልበትን ይፈጥራል ብለዋል። የጥበብ ሥራዎችና ባህል ተያያዥ መሆናቸውን ያብራሩት ወሰን ባዩ (ዶ/ር)፣ የትውልዱን ሰብዕና በመቅረጽና በባህሉ የሚኮራ ዜጋ ለማፍራት መሰል የጥበብና የመዝናኛ ሥፍራዎች ግንባታ ጉልህ ሚና ይጫወታሉ ብለዋል፡፡ እንዲሁም አዲሱ ትውልድ ጥበባዊ ሥራዎችን እንዲወድድ፣ የፈጠራ ሥራዎችን እንዲያደንቅና ሀገራዊ እሴቶቹን እንዲገነዘብ የተገነቡት ቴአትር ቤቶችና የጥበብ ስፍራዎች አስፈላጊ እንደሆኑም ተናግረዋል፡፡

ለበርካታ ዓመታት የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ከስራና ከውጥረት በኋላ ዘና የሚሉባቸው፣ ከቤተሰቦቻቸው ጋር ጥራት ያለው ጊዜ የሚያሳልፉባቸው ክፍትና ሰፊ የሕዝብ መዝናኛ ስፍራዎች (Open-air spaces) እጥረት በከፍተኛ ደረጃ ነበረባቸው። አብዛኛው የማህበራዊ መስተጋብር በተዘጋጁ ካፌዎች፣ ሬስቶራንቶች ወይም ሲኒማ ቤቶች ላይ ብቻ የተገደበ በመሆኑ፣ ነዋሪው ከተፈጥሮ ጋር የሚገናኝበት፣ አካላዊና አዕምሯዊ እረፍት የሚያገኝበት እድል ጠቦ ቆይቷል። አሁን ግን የተገነቡት ዘመናዊ ፓርኮች ይህንን ክፍተት በሰፊው በመሙላት የሰዎችን የዕለት ተዕለት የሕይወት ዘይቤ ሙሉ በሙሉ እየቀየሩት ይገኛሉ።

በተጨማሪም እነዚህ ስፍራዎች የተለያየ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዳራ ያላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ያለምንም ልዩነት የሚገናኙባቸውና እርስ በርስ የሚቀራረቡባቸው ጠንካራ የማህበራዊ ድልድይ ሆነው እያገለገሉ ነው። ሰዎች በፓርኮች ውስጥ እየተገናኙ ሐሳብ ይለዋወጣሉ፣ አዳዲስ ጓደኝነቶችን ይመስርታሉ፣ እንዲሁም የጋራ ሰላምና አንድነትን ያጠናክራሉ። በመሆኑም ፓርኮቹ የውበት ምንጭ ብቻ ሳይሆኑ፣ ጤናማ ማህበረሰብን ለመገንባትና የከተማ ነዋሪውን የሥነ-ልቦና ደህንነት ለመጠበቅ የሚጫወቱት ሚና የማይተካ ነው።

እነዚህ ፓርኮች የሀገሪቱን ባህል፣ ታሪክና ጥበብ በሚያንጸባርቅ መልኩ የተቀረጹ በመሆናቸው ለቱሪስቶች ልዩ መስህብ መሆን ችለዋል። ጎብኚዎች በፓርኮቹ ውስጥ በሚንሸራሸሩበት ወቅት የከተማዋን ዘመናዊነት እያደነቁ፣ የአካባቢውን ሰላማዊ ድባብ የመለማመድ እድል ያገኛሉ። ይህ የቱሪስቶች ፍሰት መጨመር ደግሞ ለሀገሪቱ የውጭ ምንዛሬ ግኝትና ለቱሪዝም ኢንዱስትሪው እድገት አዲስ ብርሃን ፈጥሯል።

ከመሰል የሕዝብ መዝናኛ ፓርኮች በተጨማሪ የኑሮ ውድነትን ለማቃለል፣ ምርት በብዛት ማቅረቢያ እና የግብይት ማዕከላት አካል የሆነውን ሰባተኛውን የለሚ ሁለገብ የገበያ ማዕከል ከሰሞኑ ለአገልግሎት ክፍት ተደርጓል፡፡ የገበያ ማዕከሉ የኑሮ ውድነትን የሚያቃልሉ ዘመናዊ ማሞቂያ እና ማቀዝቀዣ ያላቸው 221 መጋዘኖች፣ የችርቻሮ ሱቆች፣ ሱፐርማርኬቶች፣ ወፍጮ ቤቶች፣ በአንድ ጊዜ 250 ተሽከርካሪዎችን ማቆም የሚችል ፓርኪንግ ይዟል፤ ለለሚ ኩራ፣ ለቦሌ እና የካ ክፍለ ከተሞች ውስጥ ለሚገኙ ነዋሪዎች አማካይ ቦታ በሆነው ሰሚት ዋና መንገድ ላይ የሚገኝ ምቹ የሆነ ሁለገብ የገበያ ማዕከልን በውስጡ ይዟል ነው።

በከተማዋ የተሰሩ አካታች የልማት ፕሮጀክቶች የሕዝቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት እያረጋገጡ ይገኛሉ ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ተናግረዋል፡፡ ከልማት ፕሮጀክቶቹ ከተሰሩት ስራዎችም በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ “ገብስ ተራ” ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በሚገኘው ቁጥር 3 የበጎነት መንደርም የተገነባውን 44 የመኖሪያ ቤቶች እና ሱቆች ያሉት ባለ አምስት ወለል ህንጻ ባሳለፍነው ሳምንት ለተጠቃሚዎች የተላለፈው ትልቅ ሰው ተኮር ተግባር ነው፡፡ ገብስ ተራ ቀደም ብሎ እጅግ የተጎሳቆለ፣ ለመኖር ምቹ ያልሆነ፣ ባረጁ እና በደቀቁ ቤቶች የተሞላ፣ በተደጋጋሚ በእሳት አደጋ የሚጠቃ፣ ለአቅመ ደካማ እናቶች የማብሰያና የመጸዳጃ አገልግሎት አስቸጋሪ የነበረበት መንደር እንደነበር መረጃዎች ያሳያሉ። አሁን ላይ በአጠቃላይ 377 የመኖሪያ ቤቶች ያላቸው 5 ህንጻዎችን በመገንባት ነዋሪዎቹንም ከዛ አስከፊ አኗኗር ተላቀው፤ ክብራቸውን በሚመጥን ፅዱ፣ ዘመናዊ አኗኗር የሚፈጥር፣ ልጆች ቦርቀዉ የሚጫወቱበት እና ደረጃውን በጠበቀ መኖሪያ መንደር እንዲኖሩ መደረጉን ከንቲባ አዳነች አቤቤ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባጋሩት መልዕክት ገልጸዋል፡፡

በአብርሃም ገብሬ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review