በአዲስ አበባ የተካሄደው የዓለም ዓለቀፍ የብስክሌት ውድድር ለስፖርቱ ዕድገት አዲስ ተስፋ ይዞ መጥቷል

AMN – ግንቦት 17 ቀን 2018 ዓ.ም

በአፍሪካ ለመጀመሪያ ጊዜ በአዲስ አበባ የተካሄደውንና የዓለም አቀፉ የብስክሌት ሕብረት ዕውቅና የተሰጠው የ ሲቲ ማውንቴን ባይክ ኤሊሚኔተር ፕሮ ሊግ ውድድር አፈጻጸምን መነሻ ያደረገ የደረጃ ግምገማ ውይይት ዛሬ በአዲስ አበባ የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ቢሮ ውይይት ተካሂዷል።

በውይይቱ ላይ የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ መክዮ ሙሐመድ፣ የዓለም አቀፉ የብስክሌት ሕብረት ውድድር አዘጋጅ ክርስቶፍ ብሩሜል፣ የኢትዮጵያ ብስክሌት ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ወንድሙ ኃይሌ እንዲሁም የዘርፉ ከፍተኛ አመራሮችና ባለሙያዎች ተገኝተዋል።

በውይይቱ ላይ እንደተገለጸው፣ ባለፈው ሚያዝያ ወር መጨረሻ መዲናዋ ያስተናገደችው ይኸው ታሪካዊ ውድድር የሀገሪቱን የስፖርት መሠረተ ልማትና በጎ ገጽታ ለዓለም ለማስተዋወቅ ትልቅ አስተዋፅዖ አበርክቷል።

የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ መክዮ ሙሐመድ እንደገለጹት፤ ውድድሩ ለሀገር ውስጥ ስፖርተኞች የተስፋ ብርሃን የፈነጠቀ ከመሆኑም በላይ፣ በቀጣይ መሰል ዓለም አቀፍ ውድድሮችን በከፍተኛ ብቃት ለማዘጋጀት የሚያስችል ትልቅ ልምድ የተገኘበት ሆኖ አልፏል።

የዓለም አቀፉ የብስክሌት ሕብረት ተወካይ ክርስቶፍ ብሩሜል በበኩላቸው፣ በአዲስ አበባ የተካሄደው ውድድር እጅግ ስኬታማ እንደነበር አረጋግጠው፤ ኢትዮጵያ በያዘችው አቋምና መሠረተ ልማት በቀጣዩ የ2019 ዓ.ም የዓለምና የአህጉር አቀፍ የሲቲ ማውንቴን ባይክ ውድድርን በአፍሪካ ለመጀመሪያ ጊዜ የማስተናገድ ሙሉ አቅም እንዳላት ሕብረቱ እምነት መጣሉን ይፋ አድርገዋል።

የኢትዮጵያ ብስክሌት ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ወንድሙ ኃይሌ በበኩላቸው፣ ከሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱና ከከተማ አስተዳደሩ ጋር በመቀናጀት የተከናወነው ሥራ የዓለምን ትኩረት መሳብ የቻለ መልካም አጋጣሚ መፍጠሩን ጠቅሰው፤ በ2019 ዓ.ም የሚካሄደውን የዓለም አቀፍ የብስክሌት ሕብረት የኮንግረስ ስብሰባ እና የዓለም ዋንጫ ውድድርን በጥምረት ለማዘጋጀት የሚያስችሉ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች በመከናወን ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በቀጣይም ይፋዊ ስምምነት እንደሚፈረም ማስታወቃቸውን ከባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የማሕበራዊ የትሥሥር ገጽ የተገኘው መረጃ ያስረዳል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review