
AMN – ግንቦት 20/2018 ዓ.ም
የአሜሪካ ጦር በኢራን ላይ አዲስ ጥቃቶችን የፈጸመ ሲሆን፣ ጥቃቱ የኢራን ስትራቴጂካዊ የወደብ ከተማ በሆነችው ባንደር አባስ ላይ በሚገኝ የአንድ ወታደራዊ ተቋም ላይ ያነጣጠረ መሆኑ ተገልጿል፡፡
በጥቃቱ የኢራን ድሮኖች መመታታቸዉ የተገለጸ ሲሆን በከተማዋ በስተምስራቅ በኩል የፍንዳታ ድምፆች መሰማታቸውን የኢራን መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።
አሜሪካ በኢራን ውስጥ ባሉ ኢላማዎች ላይ ጥቃት ስትሰነዝር በሦስት ቀናት ውስጥ ይህ ለሁለተኛ ጊዜ ሲሆን፣ ጥቃቶቹን የፈጸመችው ራሷን ለመከላከል እንደሆነ ገልጻለች።
አሜሪካ በኢራን ላይ የፈጸመችዉ ጥቃት በሁለቱ ሃገራት መካከል ሲካሄድ የነበረዉን የተኩስ አቁም ስምምነት አደጋ ላይ መጣሉም ተገልጿል፡፡
ኢራን በበኩሏ አሜሪካን የተኩስ አቁም ስምምነቱን በመጣስ ጥቃት መፈጸሟን አውግዛለች።
የኢራን አብዮታዊ ጥበቃ ጦር በበኩሉ፤ ወደ ኢራን የአየር ክልል የገባን አንድ የአሜሪካንን ድሮን መትቶ የጣለ መሆኑን የገለጸ ሲሆን በአንድ ተዋጊ ጄት እንዲሁም በሌላ ድሮን ላይ ተኩስ መክፈቱን አስታውቋል፡፡ ሆኖም ድርጊቱ መቼ እንደተፈጸመ አልተገለጸም።
የአሜሪካዉ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ፤ ኢራን የቀረበዉን ስምምነት የማትቀበል ከሆነ መጠነ-ሰፊ የቦምብ ጥቃት ሊፈጸም እንደሚችል መዛታቸዉን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
በወንድማገኝ አሰፋ