AMN – ሚያዝያ 13/2018 ዓ.ም
በአሜሪካ እና በኢራን መካከል የተደረሰው የተኩስ አቁም ስምምነት ሊያበቃ ጥቂት ሰዓታት ቀርተውታል፡፡ የቴህራን ከፍተኛ ባለስልጣናት ጦርነቱ ዳግም የሚያገረሽ ከሆነ ኢራን አዳዲስ የምትመዛቸው የጦር ካርዶች እንዳሏት አሳስበዋል።
በፓኪስታኗ መዲና ኢስላማባድ ሊካሄድ ቀነ ቀጠሮ ተይዞለት የነበረው ሁለተኛው ዙር የሰላም ንግግር በሁለቱም ወገኖች በኩል እስካሁን ይፋዊ ማረጋገጫ አለመሰጠቱን ቢቢሲ በዘገባው አስነብቧል፡፡
በኢስላማባድ ጎዳናዎች ላይም ተደራዳሪዎችን ለመቀበል የተዘጋጁ ፖስተሮች እና የጸጥታ ፍተሻዎች ቢበዙም፣ በድርድሩ ዙሪያ ያለው እርግጠኝነት ግን አሁንም አነስተኛ መሆኑ ተጠቁሟል።
የኢራን ፓርላማ አባል እና አፈ-ጉባኤ የሆኑት መሀመድ ባገር ጋሊባፍ በበኩላቸው፣ ቴህራን በአሜሪካ ዛቻ እና ጫና ስር ሆና ድርድር አታደርግም ሲሉ አሥረድተዋል።
አፈ-ጉባኤው አክለውም፣ ላለፉት ሁለት ሳምንታት ግጭቱ ዳግም ከተቀሰቀሰ አሜሪካን ሊያስደነግጡ የሚችሉ አዳዲስ የጦር ስልቶች ሲነደፉ መቆየታቸውንም ጠቁመዋል።
ምንም እንኳን የአሜሪካው ምክትል ፕሬዝዳንት ጄዲ ቫንስ ለሁለተኛ ዙር ድርድር ማክሰኞ ዕለት ወደ ፓኪስታን እንደሚያቀኑ ቢናገሩም፣ የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ግን በቀጣዩ ዙር ድርድር ላይ ለመታደም ምንም ዓይነት እቅድ እንደሌላቸው መግለጫ ሰጥተዋል።
በቴህራን በኩል ስምምነቱ ኢራን ዝግጁ ያልሆነችባቸውን ከባድ መስዋዕትነቶች እንድትከፍል የሚጠይቅ ይሆናል የሚል ስጋትም ነግሷል፡፡
ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በበኩላቸው፣ ረቡዕ ዕለት የሚያበቃውን የተኩስ አቁም ስምምነት የማራዘም ዕድሉ በጣም አነስተኛ መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህም ከኢራን ጋር የሚደረገው ስምምነት በጣም በፍጥነት ሊጠናቀቅ እንደሚችል ያላቸውን እምነት የገለጹት ፕሬዝዳንት ትራምፕ፣ ይህን በተመለከተ ስለሚነሳባቸው ትችት ሲገልጹ ምንም ዓይነት ጫና እየተደረገባቸው እንዳልሆነ ሲያስተባብሉ ተደምጠዋል ሲል ቢቢሲ ዘግቧል።
በወርቅነህ አቢዮ