AMN- ሰኔ 23/2018 ዓ.ም
የስፖርት ታሪክ አብዛኛውን ጊዜ ስለ ድል እና ስለ ዋንጫ ብቻ ይነግረናል። ነገር ግን የ25 ዓመቱ ወጣት እስማኤል ሳይባሪ ታሪክ የእግር ኳስ ሜዳ ድልን ብቻ ሳይሆን በትግል እና በህይወት ተስፋ አለመቁረጥን ጭምር ያካተተ ነው።
ዛሬ በዓለም ዋንጫ ላይ ሀገሩን ሞሮኮን አኩርቶ የአትላስ አንበሶችን እየመራ ያለው ይህ ሰው፤ በአንድ ወቅት መራመድ እንኳ እንደማይችል ተነግሮት ነበር።
የስደት ጉዞ፣ የቤተሰብ ህይወት እና የልጅነት ህመም፤
የዚህ ወጣት ታሪክ የሚጀምረው ከቤተሰቦቹ ነው። የሳይባሪ ቤተሰቦች የተሻለ ህይወት ፍለጋ በመጀመሪያ ከሞሮኮ ወደ ስፔን ተሰደዱ። ሳይባሪም እ.አ.አ. ጥር 28 ቀን 2001 ስፔን ውስጥ ቴራሳ በተባለች ከተማ ተወለደ። ቤተሰቦቹ ከስፔን ወደ ቤልጂየም በመቀጠልም ወደ ኔዘርላንድስ ረጅም የስደት ጉዞ አደረጉ።

በዚህም ምክንያት ሳይባሪ የሶስት ሀገራት ዜግነት አግኝቶ ለማደግ ችሏል። ነገር ግን ትልቁ ፈተና የዜግነት ወይም የድንበር መሻገር ጉዞ ሳይሆን በራሱ አካል ውስጥ የነበረው ችግር ነበር።
ሳይባሪ የአካል እንቅስቃሴውን የገደበ ከተፈጥሮ ጋር የመጣ የጤና እክል ይዞ ተወለደ። እግሮቹ ወደ ውስጥ የተጠማዘዙ ስለነበሩ አካሉ ከልክ በላይ እየወፈረ ሲመጣ እግሮቹ ሊሸከሙት አልቻሉም።
እስከ ሁለት ዓመቱ ድረስ ለመራመድ ይቸገር ነበር። የሕክምና ባለሙያዎች ሁኔታውን አይተው ተስፋ ቆርጠው የነበረ ሲሆን ሳይባሪም ያንን ጊዜ ሲያስታውስ “እግሮቼ ወደ ውስጥ የተጠማዘዙ ስለነበሩ፣ በመሄጃ መሣሪያዎች ታግዤ እዞር ነበር፤ የሕክምና ባለሙያው ለወላጆቼ እሱ በሕይወቱ በጭራሽ ሊራመድ አይችልም”ብሎ ቤተሰቦቼን ተስፋ አስቆርጧቸው ነበር ሲል ተናግሯል፡፡
ነገር ግን ቤተሰቦቼ ተስፋ አልቆረጡም። ረጅም እና አድካሚ የሕክምና ሂደት ውስጥ አለፉ። እግሮቹን ለማስተካከል ተብለው የተሰሩ ልዩ የኦርቶፔዲክ መሣሪያዎችን በማልበስ በየቀኑ እንዲቆምና የመጀመሪያ እርምጃዎቹን እንዲራመድ ረዱት። ትግሉ ዓመታትን ቢወስድም በመጨረሻ ግን የሕክምና ባለሙያዎች “አይራመድም” ያሉት እግር መሬት መንካት ብቻ ሳይሆን ኳስ ማሳደድ ጀመረ።
ከኦርቶፔዲክ መሣሪያ እስከ PSV እና የሞሮኮ ብሔራዊ ቡድን ሳይባሪ መራመድ ከጀመረ በኋላ እግሮቹ ከእግር ኳስ ጋር አልተለዩም። ብቃቱ በታዋቂው የኔዘርላንድስ ክለብ ፒኤስቪ ኤንድሆቨን አይን ውስጥ አስገባው።

በክለቡ የወጣቶች አካዳሚ ውስጥ አጥቂ መስመር የጀርባ አጥንት በመሆን ማደግ ጀመረ።
የሞሮኮ ዋና አሰልጣኝ መሐመድ ዋህቢ ስለወጣቱ ብቃት ሲናገሩ ትልቅ አድናቆት አላቸው ፤ “ሳይባሪ ልዩ ተሰጥኦ ያለው ነው፣ በሁለቱም እግሮቹ ጎል ማስቆጠር ይችላል፣ ተከላካዮችን በቀላሉ ያጠቃል፣ ጠንካራ የመምታት ኃይል አለው፣ እንዲሁም ከፍተኛ ጥራት ያለው ተጫዋች ነው” ብለዋል።
ባለፈው ዓመት ለክለቡ ፒኤስቪ በ37 ጨዋታዎች 19 ጎሎችን በማስቆጠር የግል ክብረ ወሰኖቹን አሻሽሏል።
በዚህም ስራው የኤረዲቪዚ የዓመቱ ምርጥ ተጫዋች ሽልማትን ያሸነፈ ሲሆን፣ ክለቡ ፒኤስቪ የሊጉን ዋንጫ በተከታታይ ለሶስተኛ ጊዜ እንዲያገኝ አስችሏል።
የዓለም ዋንጫ ታሪክ እና የድል ጉዞ ይህ የክለብ ስኬት ወደ ሞሮኮ ብሔራዊ ቡድን አሻገረው።
ከሞሮኮ ብሔራዊ ቡድን የቀረበለትን የመጀመሪያ ጥሪ ተቀብሎ ወደ ሜዳ ሲገባ አዲስ ታሪክ ለመስራት እንደሆነ ማንም አልረሳውም።
ከጠንካራው የብራዚል እግር ኳስ ቡድን ጋር ባደረጉት የመጀመሪያ ጨዋታ የመጀመሪያውን ጎል አስቆጠረ። ከዚያ በኋላ ከስኮትላንድ ጋር ባደረጉት ውድድርና በሀይቲ ላይ ጎል በማስቆጠር መላውን ዓለም አስገረመ።

ሳይባሪ በ3 የምድብ ጨዋታዎች 3 ጎሎችን በማስቆጠር ቡድኑን ወደ ቀጣዩ ዙር እንዲያልፍ በማድረግ ከኔዘርላንድስ ጋር ለመግጠም ተገደደ፡፡ ጨዋታው ከፍተኛ ጫና እና ውጥረት የበዛበት ሲሆን ከኔዘርላንድስ ተጫዋች ጋር እስከ መድማት የደረሰ ግጭትም ተከስቶ ነበር።
በዚህ ጨዋታ 1 ለ 1 የተለያዩት ሁለቱ ሀገራት፣ የመጨረሻውን እና በጣም ወሳኙን የፍፁም ቅጣት ለመምታት ተዘጋጁ፡፡ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ደጋፊዎች በስታዲየም በሚሊየኖች የሚቆጠሩ ደግሞ በቴሌቪዥን የቅጣት ምቱን በጉጉት ሲጠብቁ ነበር፡፡
ሳይበሪ የቅጣት ምቱን ለመምታት ቀረበ፤ በዚያ ከባድ ጫና ውስጥ እግሮቹ እንደልጅነቱ አልተንቀጠቀጡም። ቀጥተኛ እና ኃይል ባለው ምት ጎሉን አስቆጠረ።
ያ ውጥረት ወደ ንፁህ ደስታ ተቀየረ። የአትላስ አንበሶች ጀግኖች ሆነው ወጡ። እስማኤል ሳይባሪ ዛሬም ሆነ ለዘላለም በሞሮኮ እግር ኳስ ታሪክ ውስጥ እንደ አንድ ጀግና ተወድሶ ቀርቷል።
የሳይባሪ ታሪክ በሜዳ ላይ የሚቆጠር ጎል ብቻ ሳይሆን፣ ‘ተስፋ አለመቁረጥ’ ማለት ምን ማለት እንደሆነ ማሳያ ሆኗል፡፡
በወንድማገኝ አሰፋ