AMN ግንቦት 20 ቀን 2018 ዓ/ም

ወንጀሉ የተፈፀመው ግንቦት 19 ቀን 2018 ዓ/ም በአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ 01 ልዩ ቦታው ቴድሮስ አደባባይ አከባቢ ነው።
ተጠርጣሪዎቹ ናትናኤል ሄኖክ እና ብርሀን ተስፋዬ የተባሉ ሲሆኑ ኮድ 3C 06 5 52 A.A ሱዚኪ ዲዛየር ተሽከርከሪ በመያዝ በሰዎች ልብስ ላይ ፈሳሽ በመድፈትና የሚጠርጉ በመምሰል የስርቆት ወንጀል ሲፈጽሙ ነበር።
የግል ተበዳይ ኮኪ ኪፒያማ ጃቻናዊ ዜግነት ያለው እና ለጉብኝት ወደ ኢትዮጵያ የመጣ ሲሆን ካረፈበት ሆቴል ይወጣል።
ናትናኤል ሄኖክ ከተሽከርካሪው ኋላ ወንበር በመቀመጥ እና ብርሀን ተስፋዬ ደግሞ የመኪናዉ አሽከርካሪ በመሆን ከግል ተበዳይ አጠገብ መኪናቸውን ያቆማሉ።

ናትናኤል ሄኖክ የመኪናውን መስኮት በመክፈት የዳሽ ቦርድ ማፅጅያ ፈሳሽ በግል ተበዳይ ልብስ ላይ ይደፋል።
ተጠርጣሪውም መኪናውን ከፍቶ በመውጣት ይቅርታ በማለት የግል ተበዳይ ልብስ በውሃ እያደረገ በመጥረግና ትኩረቱን በማሳጣት ከኪሱ አይፎን 17 ፕሮማክስ የዋጋ ግምቱ 206 ሺ የሚያወጣ ሞባይል ስልክ ስርቆት ፈፅመው ይሰወራሉ።
የግል ተበዳይ ትንሽ እንደተራመደ ኪሱን ሲፈትሽ ስልኩ የለም።
ቶሎ ወደ ሆቴሉ በመመለስ ለሆቴሉ ባለቤት ስርቆት እንደተፈፀመበት በማስረዳት ለፒያሳ ፖሊስ ጣቢያ ያሳውቃል።
የወንጀል መከላከል አባሎች በቦታው ላይ በመገኘት በግል ተበዳይ ስልክ ጂፒኤስ በመከታተል ተጠርጣሪዎቹ አዲስ ከተማ ይርጋ ኃይሌ አካባቢ አንድ ሰዓት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ በቁጥጥር ስር ውለዋል፡፡

በተሽከርካሪያቸው ላይ ፍተሻ ሲደረግም ከግል ተበዳይ የተሰረቀ ስልክና ሌላ ተጨማሪ 4 ስማርት ሞባይል ስልኮች ተይዘዋል።
ከተያዙ ስልኮች መካከልም የአንድ የግል ተበዳይ ወደ ስልኩ ሲደውል ፖሊስ ስልኩን በማንሳት እንደተሰረቀ ይገልጽለታል።
ፖሊስ የግል ተበዳይ ባለበት በመሄድና ወደ ጣቢያ በማስመጣት: የግል ተበዳይም ስልኩንና ተከሳሾች በመምረጥ በቦሌ ሚካኤል አካባቢ ተመሳሳይ ድርጊት ፈፅመውበት እንደነበር ተናግረዋል።
በአራዳ ክፍለ ከተማ ፖሊስ ዋና መምሪያ የፒያሳ ፖሊስ ጣቢያ ባለቤቶቻቸው ያልታወቁና ከተጠርጣሪዎቹ የተገኙ አምስት (5) ስልኮች ባለቤቶችን እያፈላለገ ነዉ።
በተጠርጣሪዎቹ ተመሳሳይ ወንጀል የተፈፀመባቸው ግለሰቦች በፖሊስ ጣቢያው በመቅረብ ስልኮቻቸውን መረከብ እንደሚችሉም የአዲስ አበባ ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ለኤኤምኤን በላከዉ መረጃ መልዕክቱን አስተላልፏል፡፡