AMN-ግንቦት 21/2018 ዓ.ም

የኢትዮጵያን ዲሞክራሲያዊ ጉዞ አዲስ ምዕራፍ ያሰምራል ተብሎ የሚጠበቀው 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ነጻ፣ ግልጽና ተአማኒ እና አካታች እንዲሆን የአፍሪካ ህብረትን ጨምሮ ልዩ ልዩ አህጉራዊ ተቋማት ታሪካዊና ጠንካራ አጋርነታቸውን በተግባር እያሳዩ ይገኛሉ።
እነዚህ ተቋማት ቡድኖቻቸውን በማሰማራት የምርጫውን ሂደት ለመታዘብ ሙሉ ዝግጅታቸውን ማጠናቀቃቸውን ገልጸዋል። ይህም ለአፍሪካውያን ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሄ የሚለውን መርህ የሚያረጋግጥ ነው።

ግንቦት 24/2018 ዓ.ም ለሚካሄደው 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ስኬታማነት የአፍሪካ ህብረት እና በምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት ባለሥልጣን (ኢጋድ) የሀገሪቱን ዲሞክራሲያዊ ተቋማት ወደ ላቀ ደረጃ ከማሸጋገሩም በላይ ለአጠቃላይ ቀጠናው ሰላምና መረጋጋት ጠቀሜታ አለው፡፡

የአፍሪካ ተቋማት በምርጫው ሂደት ላይ የሚኖራቸው ተሳትፎ በዋናነት፤ የአህጉሪቱ ታዛቢዎች በቦታው ተገኝተው የምርጫውን ሂደት ዓለም አቀፍና አህጉራዊ መስፈርቶችን የጠበቀ እንዲሆን እና ተአማኒነትን ለማጠናከር ይጠቅማል፡፡
በኢትዮጵያ የሚገነባው ሰላምና ዲሞክራሲ ለቀጠናውም ሆነ ለጠቅላላው አህጉር የሚኖረውን ጠቀሜታ በመረዳት አጋርነታቸውን በተግባር ማረጋገጣቸውን ያሳያል። የአፍሪካ ተቋማት ለዚህ ምርጫ የሰጡት ትኩረትና ያሳዩት ዝግጅት አህጉሪቱ በራሷ መንገድ ጠንካራና ተቋማዊ ዲሞክራሲን ለመገንባት የጀመረችውን ጉዞ የሚያፋጥን ትልቅ እርምጃ ነው።

ታዛቢዎቹ የድምፅ አሰጣጥ ሂደቱን ጨምሮ የድምፅ ቆጠራውን ፍትሃዊ መሆን በቅርበት የሚታዘቡ ይሆናል። ይህ የአፍሪካዊ ተቋማት አጋርነት ተሳትፎ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሂደቱን ሙሉ በሙሉ ገለልተኛና ግልጽ በሆነ መንገድ ለመምራት ለሚያደርገው ጥረት አጋዥ ከመሆኑም ባሻገር ምርጫው በሰላም ተጀምሮ በስኬት እንዲጠናቀቅና የሕዝብ ድምፅ የሚከበርበት ሥርዓት እንዲሰፍን የበኩሉን አዎንታዊ አሻራ ያኖራል።
በፍሬሕይወት ብርሃኑ