AMN- ሰኔ 7/2018 ዓ.ም

በቡድን በመደራጀትና ጨለማን ተገን በማድረግ የመሰረተ ልማት አውታሮች ላይ የስርቆት ወንጀል የፈፀሙ 5 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታወቀ፡፡
የወንጀል ድርጊቱ የተፈፀመው በልደታ ክ/ከተማ ወረዳ 6 ራሺያ ካምፕ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ነው።

ተጠርጣሪዎቹ ጨለማን እንደምቹ አጋጣሚ በመጠቀም ከሌሊቱ 7 ሠዓት አካባቢ ለቴሌኮም አገልግሎት የሚውል ከመሬት ስር የተዘረጋ ኬብል በተለያዩ መቁረጫዎች በመቆራረጥ ይዘው ከአካባቢው ሊሰወሩ ሲሞክሩ በስራ ላይ በነበሩ የፖሊስ አባላትና የአካባቢ ጥበቃዎች ትብብር ከነ ኤግዚቢቱ በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተካሄደ መሆኑን በልደታ ክ/ከተማ ፖሊስ ዋና መምሪያ የመከኒሳ አካባቢ ፖሊስ መምሪያ ገልጿል።
ፖሊስ በተጠርጣሪዎቹ ላይ ተገቢውን ምርመራ የማስፋት ተግባር እያከናወነ መሆኑን ገልጾ በቀጣይ ክስ እንደሚመሰርትም ጠቁሟል።
በመሰረተ ልማት ላይ የሚፈፀም ወንጀል ሀገርን ለከፍተኛ ኪሳራ የሚዳርግ ተግባር በመሆኑ ህብረተሰቡ መሰል የወንጀል ድርጊቶችን ሲመለከት በአካባቢው ለሚገኝ የጸጥታ ኃይል ጥቆማ መስጠት እንዳለበት የአዲስ አበባ ፖሊስ መልእክት አስተላልፏል።