AMN – ሰኔ 7/2018 ዓ.ም

የአንድ ዘመናዊ ከተማ እድገትና ስልጣኔ ከሚለካባቸው ዋነኛ መመዘኛዎች መካከል ለነዋሪዎች ምቹ እና ጤናማ አካባቢን መፍጠር መቻል በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳል።
ይህንን ዓለም አቀፋዊ የከተሞች ልማት መርህ መሰረት በማድረግ አዲስ አበባ የነዋሪዎችን ሁለንተናዊ የአኗኗር ዘይቤ ለማሻሻል የሚያስችሉ ሰፊና ዘመናዊ የገፅታ ግንባታ ስራዎችን እያከናወነች ትገኛለች።

ቀደም ባሉት ጊዜያት በከተማዋ ለስፖርታዊ እንቅስቃሴና ለመዝናኛ የሚሆኑ ቦታዎች እጥረት መኖሩ ለነዋሪዎች፣ በተለይም ለወጣቶች እና ለህፃናት ትልቅ ተግዳሮት ሆኖ መቆየቱ ይታወሳል።
ሆኖም ባለፉት ጥቂት ዓመታት ለኑሮ ምቹ ያልሆኑ እና ለተለያዩ ስጋቶች ተጋለጠው የነበሩ አካባቢዎችን በመቀየር ዘመናዊ፣ ማራኪ እና ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ በርካታ የስፖርት ማዘውተሪያ እና የመዝናኛ ፓርኮችን በመገንባት ረገድ ከፍተኛ እንቅስቃሴ ተደርጓል።

በዚህም የመዲናዋ ነዋሪዎች በነፃነት ብስክሌት የሚነዱባቸው፣ ዘመናዊ የስፖርት እንቅስቃሴ የሚያደርጉባቸው፣ እንዲሁም የእረፍት ጊዜያቸውን በተፈጥሮ በታጀበ አረንጓዴ ስፍራ የሚያሳልፉባቸው መዝናኛ ስፍራዎች በስፋት ተገንብተዋል።

ኢትዮጵያ በዓለም አደባባይ ያላትን የአትሌቲክስ ታሪክ የሚመጥኑ ስፍራዎች መገንባታቸው፤ ከተማዋ በስፖርት ቱሪዝም ተጠቃሚ እንድትሆን፣ የውጭ ምንዛሬ እንድታስገባ እና ያላትን ገፅታ ለዓለም እንድታስተዋውቅ ጉልህ ሚና እየተጫወተ ይገኛል።
ለዚህም በዋናነት ለተለያዩ ዓለም አቀፍ የስፖርት ውድድሮች ምቹ ሆኖ የተሰራውና ኢትዮጵያን በዓለም መድረክ ከፍ ያደረጉ ጀግኖች አትሌቶችን በክብር የሚዘክረው አዲስ ስፖርት ፓርክ ማሳያ ነው።

በከተማዋ እምብርት ላይ አረንጓዴነትን ከዘመናዊ የከተማ መዝናኛ ጋር አዋህዶ የያዘው የአራዳ ፓርክ ሌላኛው ማራኪ ስፍራ ሲሆን ከሌሎች አገልግሎቶች ባሻገር በኢትዮጵያ የመጀመሪያ የሆነውን የስፖርት አሬና አካቷል።
እንዲሁም የእንጦጦ-ቀጨኔ የወንዝ ዳርቻ ልማት ለአእምሮ እና ለአካል ብቃት እንቅስቃሴ ምቹ ሆኖ የተገነባ ሲሆን የተሽከርካሪ፣ የሳይክል፣ የእግረኛ እና የተራራ ላይ ጉዞ መንገዶችን፣ እንዲሁም ሌሎች የመዝናኛ ስፍራዎችን አጣምሮ ይዟል።

በመዲናዋ በሚገኙ የተለያዩ ፓርኮች እና በሁሉም ክፍለ ከተሞች የተገነቡት የስፖርት ማዘውተሪያ እና የመዝናኛ ስፍራዎች የከተማዋን ውበት ከመጨመር ባለፈ የነዋሪውን የአኗኗር ዘይቤ እየቀየሩ መሆናቸውን መረጃዎች ያሳያሉ፡፡
በትዝታ መንግስቱ
See less