የኢትዮጵያ እና የካሜሮን የ60 ዓመት የዲፕሎማሲ ግንኙነት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተገለጸ

AMN- ሰኔ 8/2018 ዓ.ም

ረጅም ዓመታትን ያስቆጠረው የኢትዮጵያ እና የካሜሮን የ60 ዓመት የዲፕሎማሲ ግንኙነት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል በኢትዮጵያ የካሜሮን አምባሳደር ጃክዊስ ንዶምቤ ገለጹ፡፡

በኢትዮጵያ የካሜሮን ኤምባሲ ሰራተኞች ካሜሮን ኤምባሲዋን በኢትዮጵያ የከፈተችበትን 60ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ በአዲስ አበባ ጎዳናዎች የእግር ጉዞ አድርገዋል።

በዚሁ ወቅት በኢትዮጵያ የካሜሮን አምባሳደር ጃክዊስ ንዶምቤ፤ በአውሮፓውያኑ አቆጣጠር 1966 የተጀመረው የሁለቱ ሀገራት የዲፕሎማሲ ግንኙነት ዛሬ ላይ 60 ዓመታትን አስቆጥሯል ብለዋል፡፡

በእነዚህ ዓመታት ከዲፕሎማሲው ባለፈ በተለያዩ ዘርፎች ውጤታማ ስራዎችን መስራት እንደተቻለ አንስተዋል፡፡

ሀገራቱ በርካታ የሁለትዮሽ ስምምነቶችን በማድረግ በኢኮኖሚው ያላቸውን ግንኙነት ፍሬያማ ማድረግ ችለዋልም ብለዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም አሁን ላይ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በሳምንት 14 ጊዜ ወደ ካሜሮን በረራ እያደረገ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡

ይህም ከኢኮኖሚው ባለፈ የሁለቱን ሀገራት ዜጎች በማቀራረብ በኩል ጉልህ ሚና እንዳለው ተናግረዋል፡፡

ረጅም ዓመታትን ያስቆጠረው የኢትዮጵያ እና የካሜሮን ግንኙነት በቀጣይም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አምባሳደሩ ጠቁመዋል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ ጎዳናዎች ላይ የተደረገው የእግር ጉዞም ጤናን ከመጠበቅ ባሻገር የሀገራቱን ግንኙነት ለማጠናከር አላማ ያደረገ ነው ያሉት የጉዞው ተሳታፊዎች በበኩላቸው፣ በተለይ የከተማዋን ፈጣን እድገትና ውበትም አድንቀዋል።

በዚህም አፍሪካውያን ከሰራን መለወጥና ማደግም እንደምንችል አዲስ አበባ ማሳያ ናትም ሲሉ ገልጸዋል፡፡

አፍሪካውያን ችግሮቻችንን በራሳችን መፍታትና በራሳችን ዜጎችም መለወጥ እንደሚቻል በአዲስ አበባ ከተማ የተሰራውን ስራ ማየት በቂ ነው ያሉት ተሳታፊዎቹ፣ ይህም በካሜሮንና በሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ጭምር ልምድ የሚወሰድበት ነው ብለዋል።

አፍሪካውያን መነጣጠል ሳይሆን ዲፕሎማሲን በማጠናከርና በመተባበር አብሮ ማደግ እንዳለባቸውም መልእክት አስተላልፈዋል፡፡

በየሻምበል ምህረት

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review