በፖርኮችና መዝናኛ ሥፍራዎች ልጆችን እያጫወቱ አብሮ መዝናናት አዲሱ የመዲናዋ ገጽታ

AMN ሰኔ 11/2018 ዓ.ም

በመዲናችን አዲስ አበባ ቅዳሜና እሁድን ጨምሮ አመሻሽና በሌሎች የአዘቦት ቀናት በኮሪደርና ወንዝ ዳርቻ ልማት በየአካባቢው በተገነቡ የመዝናኛ ሥፍራዎች ከልጆቻቸው ጋር አብረው የሚጫወቱ ወላጆችን ፣ አሳዳጊዎችን ፣ አዛውንቶችንና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎችን መመልከት የተለመደ ሆኗል፡፡

ትናንት ከትምህርት ቤት ውጪ በጋራ ለመጫወት ፣ ለመነጋገርና ለመማማር እድል ያላገኙ ህጻናትና ታዳጊዎች በአቅራቢያቸው በተገነቡ የመዝናኛ ፣ የስፓርትና የማረፊያ ሥፍራዎች እርስ በርስ ተገናኝተው ለመጫወት እድል አግኝተዋል፡፡

በሥራና በሌሎች ምክንያቶች ማለዳ ወጥተው ከመሸ በኋላ ወደ ቤታቸው የሚገቡ ፤ ከቤተሰቦቻቸውና ከጎረቤቶቻቸው ጋር ለመገናኘት ጊዜ ያላገኙ የመዲናዋ ነዋሪዎችም በነዚህ የእረፍት ቀናት ከቤታቸው ወጣ ብለውና ተሰባስበው ልጆቻቸውን እያጫወቱ ራሳቸውም የሚዝናኑበትን አጋጣሚ አግኝተዋል፡፡

በአዲስ አበባ የተከናወኑ እና በመከናወን ላይ የሚገኙ በርካታ የልማት ሥራዎች አካታችና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ያደረጉ መሆናቸው እና ከሁሉም በላይ የነገ ሃገር ተረካቢ ህጻናትና ወጣቶችን ማዕከል ያደረጉና ከአሁን ቀደም ያልተለመዱ መሆናቸው ደግሞ ልዩ ያደርጋቸዋል፡፡

ከከተማ አስተዳደሩ ያገኘነው መረጃ እንደሚያሳየው በአዲስ አበባ ከተማ በአሁኑ ወቅት ከ5ሺህ በላይ የልጆች መጫወቻዎች ፣እንክብካቤ የሚያገኙበት ከ1ሺ በላይ የሕጻናት ማቆያዎች ተገንብተው አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኙ ሲሆን ሕጻናት ከአካባቢያቸው ሳይርቁ ከወላጅና አሳዳጊዎቻቸው ጋር ተደስተውና ቦርቀው ለመጫወት እድል አግኝተዋል፡፡

የተገነቡት የልጆች መጫወቻ ሥፍራዎች ዘመናዊና በአይነታቸው ልዩ ከመሆናቸውም በላይ ሕጻናት እየተዝናኑ ለመማማር የሚያግዙ ናቸው፡፡

በተለያዩ ፓርኮች የተገነቡት የሕጻናት መጫወቻና የስፓርት ማዘውተሪያዎችም ቢሆኑ ለአእምሮ እና ለአካል ብቃት እንቅስቃሴ ምቹ ሆነው የተገነቡ ናቸዉ፡፡

የበጎነት መንደርን ጨምሮ በተለያዩ አካባቢዎች የተገነቡ እነዚህ መሰረተ ልማቶችም ከሁሉም በላይ ሕጻናትና ወጣቶችን ማዕከል ያደረጉ መሆናቸው የከተማ አስተዳደሩ ለትዉልድ ግንባታ የሰጠውን ልዩ ትኩረት የሚያረጋግጥ ነው፡፡

የከተማ አስተዳደሩ ወጣቶች በአእምሮና በአካል የዳበሩ እንዲሆኑ የስፖርት ማዘውተሪያዎችን ከመገንባት ባለፈ ትላልቅ ስታዲየሞችንም በመገንባት ላይ ይገኛል፡፡

በወንድማገኝ አሰፋ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review