AMN-ሰኔ 11/2018 ዓ.ም
በሰሜን ኢትዮጵያ ያለውን ሰላምና ደህንነት በድጋሚ ከፍተኛ አደጋ ላይ እንዲወድቅ እየሰሩ ናቸው ባላቸው ፅንፈኛ የሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሃት) አካላት ላይ የቪዛ ዕገዳ ርምጃ መወሰዱን በኢትዮጵያ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ በይፋዊ የፌስቡክ ገጹ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሩቢዮ በኢሚግሬሽን እና ዜግነት ሕግ በተሰጣቸው ሥልጣን መሠረት፣ በፅንፈኛ የህወሃት አባላት እና በቅርብ የቤተሰብ አባሎቻቸው ላይ የቪዛ ገደብ እንዲጣል መወሰናቸው ተመላክቷል። ውሳኔው በትግራይ ክልል ያለውን ቀውስ ለመፍታት የሚደረገውን ጥረት በማደናቀፍ ረገድ ተጠያቂ በሆኑ ወይም በተባባሪነት በተሳተፉ ግለሰቦች ላይ ያነጣጠረ ነው።
ዩናይትድ ስቴትስ በሰላምና በክብር መኖር ከሚፈልገው ከመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጎን መቆሟንም ገልጻለች። በክልሉ መረጋጋትን አደጋ ላይ የሚጥሉ አካላትን ተጠያቂ ለማድረግም ጥረት እንደምታደርግ አስታውቃለች።