አሜሪካ እና ኢራን በስዊዘርላንድ የሚያደርጉት ድርድር ዘላቂ ሰላም ያመጣ ይሆን?

You are currently viewing አሜሪካ እና ኢራን በስዊዘርላንድ የሚያደርጉት ድርድር ዘላቂ ሰላም ያመጣ ይሆን?

AMN – ሰኔ 14/2018 ዓ.ም

አሜሪካ፤ እስራኤልና ኢራን በመካከለኛዉ ምስራቅ ከወራት በፊት የጀመሩት ጦርነት ለራሳቸዉ ብቻ ሳይሆን ለቀጣናዉና ለተቀረዉ አለም እንቆቅልሽ ሆነ ቀጥሏል፡፡

እርስ በርስ ከመወነጃጀል አልፈዉ ለመደራደርና ተኩስ ለማቆም ተስማምተናል ብለዉ በተደጋጋሚ መግለጫ የሚያወጡት እነዚህ ሃገራት ከጥቂት ቀናት ቆይታ በኋላ ዳግም ወደ ግጭት በመመለስ ራሳቸዉ ግራ ተጋብተዉ አለምን ግራ አጋብተዋል፡፡

የመካከለኛዉ ምስራቅ ዋንኛ የግጭትና የድርድር አካል የሆነችዉ የሆርሙዝ ወሽመጥ በተደጋጋሚ ተከፍታ በተደጋጋሚ ተዘግታለች፡፡

የአሜሪካው ምክትል ፕሬዝዳንት ጄዲ ቫንስ እና በኢራኑ ዋና ተደራዳሪ መሀመድ ባቄር ቃሊባፍ የሚመራው የሰላም ንግግር ልዑክ ለድርድር ጄኔቫ በገባበት በዚህ ሰአት ኢራን የሆርሙዝ ወሽመጥን ዳግም መዝጋቷን አሳዉቃለች፡፡

አሜሪካ እና ኢራን ለድርድሩ የሚሆን የ60 ቀናት የተኩስ አቁም ስምምነት አድርገው የነበረ ቢሆንም፣ እስራኤል በሊባኖስ ላይ ባደረሰችዉ ጥቃት ምክንያት ነዉ የኢራን አብዮታዊ ዘብ በምላሹ የሆርሙዝን ወሽመጥ የዘጋዉ፡፡

ይህም ሆኖ የአሜሪካ ጦር የንግድ መርከቦች ግን በእንቅስቃሴ ላይ መሆናቸዉ ነዉ የተሰማዉ፡፡

ሁለቱም ወገኖች በፓኪስታን የተዘጋጀዉን እና በፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ እና በፕሬዝዳንት መስዑድ ፔዜሽኪያን የተፈረመውን ጊዜያዊ ስምምነት ወደፊት ለማስቀጠል እንደሚፈልጉ ተዘግቧል፡፡

የአሜሪካዉ ምክትል ፕሬዝዳንት ጄዲ ቫንስ ለድርድሩ ወደ በስዊዘርላንድ ከመጓዛቸዉ በፊት ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ በኑክሌር ጉዳይ እና በሊባኖስ የተኩስ አቁም ዙሪያ መሻሻል እንደሚኖር ተስፋ አደርጋለሁ ብለዋል፡፡

የኢራን አብዮታዊ ዘብ በበኩሉ እስራኤል በሊባኖስ ላይ የፈጸመችው ጥቃት አሜሪካ ለተኩስ አቁሙ የገባችውን ቃል እንደ መጣስ ይቆጠራል ሲል ከሷል፡፡

የኢራኑ የበላይ መሪ አያቶላ ሙጅተባ ኻሜኒ አማካሪ የሆኑት መሀመድ ሞክበር፣ አሜሪካ ሊባኖስን ጨምሮ በሁሉም ግንባሮች የተኩስ አቁሙን የመጀመሪያ ስምምነት ተግባራዊ ማድረግ ተስኗታል ሲሉ መክሰሳቸዉን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡

ስምምነቱ በተጨባጭ ወደ ተግባር ካልተቀየረ የመካከለኛው ምስራቅ የኃይል አቅርቦት ፍሰት እንደተገደበ ይቆያል ሲሉ አክለዋል።

አሜሪካ፤ እስራኤልና ኢራን በተደጋጋሚ እየተስማሙ መልሰዉ የሚያፈርሱት የመካከለኛዉ ምስራቅ የሰላም ድርድር በምን መልኩ ይጠናቀቅ ይሆን የሚለዉ ጥያቄ አሁንም የበርካቶች መነጋገሪያ ሆኗል፡፡

በወንድማገኝ አሰፋ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review