የሊዮኔል ሜሲ ፣ ኪሊያን ምባፔ እና ኧርሊንግ ሃላንድ የዓለም ዋንጫ

You are currently viewing የሊዮኔል ሜሲ ፣ ኪሊያን ምባፔ እና ኧርሊንግ ሃላንድ የዓለም ዋንጫ

AMN-ሰኔ 16/2018 ዓ.ም

በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ 48 ሀገራት እየተሳተፉበት የሚገኘው 23ኛው የዓለም ዋንጫ የፉክክር ግለቱ መሰማት ጀምሯል። ያልተጠበቁ ውጤቶች ፤ ያልተገመቱ የቡድን ብቃቶች የውድድሩ ጥዓም ሆነው የስፖርቱ ወዳድ ከምንጊዜም በላይ ጨዋታዎቹን ለመከታተል እንዲነሳሳ አድርጓል።

የብሔራዊ ቡድኖች ዋንጫ ለማንሳት ከመሯሯጥ እኩል የውድድሩ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ለመሆን እየተደረገ ያለው ትንቅንቅ የበርካቶችን ቀልብ ስቧል።

ሊዮኔል ሜሲ ፣ ኪሊያን ምባፔ እና ኧርሊንግ ሀላንድ የፉክክሩ ዋነኛ ተዋንያን ናቸው። እያንዳንዳቸው ሁለት ጨዋታ ላይ የተሳተፉት ሦስቱ ኮከቦች በጋራ 13 ግቦችን አስቆጥረዋል።

አርጀንቲናዊው ድንቅ ሊዮኔል ሜሲ አምስት ግቦችን በማስመዝገብ የበላይነቱን ወስዷል። ነገ 39 ዓመት የሚሞላው የኢንተር ሚያሚው ተጫዋች በዚህ የዓለም ዋንጫ ስለመሳተፉ እራሱም እርግጠኛ አልነበረም። በኳታሩ የ2022ቱ ዓለም ዋንጫ ሀገሩን ለሦስተኛ የዓለም ዋንጫ ድል ካበቃ በኋላ በርካቶች ከብሔራዊ ቡድኑ ጋር ይለያያል ብለው ጠብቀው ነበር።

በኢንተር ሚያሚ ያሳለፋቸው ግሩም ዓመታት እንዲሁም ብሔራዊ ቡድኑ አሁንም የእርሱ ጥገኛ መሆኑ ሀገሩን ለመወከል እንዲወስን አድርጎታል።

ለአርጀንቲናውያን እንዲሁም ለእግርኳስ አፍቃሪያን የሜሲ ውሳኔ አስደሳች ነበር።

ከዓመታት በፊት እንደነበረው ፈጣን ባይሆንም ፣ ሦስት አራት ተጫዋቾችን የማለፍ አቅሙ ባይኖረውም ሌሎች የሌላቸው አእምሮአዊ ቅልጥፍና ግን ይዟል።

ሜዳ ላይ እንደእርሱ ለፍፁምነት የቀረበ ውሳኔ የሚያሳልፍ ተጫዋች የለም። አሁንም ሀገሩን ተሸክሞ እስከ ቻለው ድረስ ለመጓዝ ተዘጋጅቷል።

የአባቱን ሆርጌ ሜሲ የጠና ህመም በውስጡ ይዞ እየተጫወተ የሚገኘው የቀድሞ የባርሰሎና ታላቅ ተጫዋች ፣ አርጀንቲና ያለ እርሱ ከባህር የወጣ አሳ እንደሆነች ዳግም አሳይቷል።

ደቡብ አሜሪካዊቷ ሀገር አልጄሪያን 3ለ0 ፣ ኦስትሪያን 2ለ0 ስታሸንፍ የተቆጠሩት ግቦች ሁሉም የተመዘገቡት በሊዮኔል ሜሲ ነው።

ስድስተኛ የዓለም ዋንጫ ተሳትፎውን እያደረገ የሚገኘው ሜሲ በውድድሩ ያስቆጠራቸው ግቦች 18 ደርሰዋል። ጀርመናዊው የቀድሞ አጥቂ ሚረስላቭ ክሎሰ ለ12 ዓመታት ይዞት የቆየውን የ16 ግቦች ክብረወሰንን አሻሽሎ ብቻኛ የታሪኩ ባለቤት ሆኗል።

አሜሪካ ፣ ሜክሲኮ እና ካናዳ በጋራ እያሰናዱት ባለው የዓለም ዋንጫ ድምቀት የሆነው ሊዮኔል ሜሲ ብቻ አይደለም ፤ ኪሊያን ምባፔ እና ኧርሊንግ ሀላንድ እኛም አለን እያሉ ነው።

በ27 ዓመቱ ሦስተኛ የዓለም ዋንጫውን እየተሳተፈ የሚገኘው ኪሊያን ምባፔ አራት ግቦች አሉት። ፈረንሳይ ሴኔጋል እና ኢራቅን በረታችባቸው ጨዋታዎች ላይ ሁለት ሁለት ግቦችን አስቆጥሯል።

ከዚህ ቀደም በተሳተፈባቸው ሁለት የዓለም ዋንጫዎች 12 ግቦች የነበሩት የሪያል ማድሪዱ አጥቂ የግብ መጠኑን 16 አድርሶ ሊዮኔል ሜሲን ለመፎካከር ዝግጁ እንደሆነ አሳይቷል።

የሜሲ እና የምባፔ በሁለት ግብ ብቻ መለያየት እያንዳንዱ የሚሳተፉባቸው ጨዋታዎች በጉጉት እንዲጠበቁ አድርጓል።

የመጀመሪያ የዓለም ዋንጫውን እየተሳተፈ የሚገኘው ኧርሊንግ ሀላንድ እድሉን ካገኘ በታላቅ መድረክ ላይ ጎልቶ መውጣት እንደሚችል አሳይቷል።

የ25 ዓመቱ ኖርዌያዊ አጥቂ ሀገሩን በትልቅ መድረክ ሲወክል የመጀመሪያው ቢሆንም ጠንቅቆ የሚያውቀው ግብ የማስቀጠር ተግባሩን አልረሳም። መድረኩ ገዝፎበት በራስ መተማመኑን አጥቶ የመረቡ አቅጣጫ አልጠፋበትም።

ይልቅ ከ28 ዓመት በኋላ ወደ ዓለም ዋንጫ የተመለሰችው ሀገሩን ወደ ጥሎ ማለፍ ዙር እንድትገባ የረዱ አራት ግቦችን ኢራቅ እና ሴኔጋል ላይ አስቆጥሯል።

የማንችስተር ሲቲው አጥቂ ሀገሩን ከመርዳት ውጪ በግሉ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ሆኖ ለመጨረስ እየተጋ ይገኛል። በቀጣይ ፈረንሳይ ከኖርዌይ ሲጫወቱ ምባፔ እና ሃላንድ የሚያሳዩት ብቃት በጉጉት ይጠበቃል።

የውድድሩ ሌላ ድምቀት ከሆኑት ሦስት ተጫዋቾች ውስጥ ማን ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ሆኖ ይጨርሳል? ግምትዎን ያድርሱን!

በሸዋንግዛው ግርማ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review