AMN – ሰኔ 16/2018 ዓ.ም
ጊዜው እኤአ መጋቢት 2001 ነው ፤ ልምምድ ላይ የነበረ አንድ ተጫዋች ተዝለፍልፎ ወደቀ።
የቡድኑ ዶ/ር ፍራንክ ኦዴጋርድ እየተጣደፈ የወደቀው ተጫዋች ጋር ደረሰ። ያየው ነገር ስሜት የሚረብሽ ሆነበት ፤ ድምፁን ከፍ አድርጎ አምቡላንስ እንዲጠራ ጠየቀ።
የቡድን አጋሮቹ በሁኔታው ተደናገጡ፤ ድብልቅልቅ ያለ ስሜት ፣ ትርምስ የበዛበት እንቅስቃሴ ታየ። ዶክተሩ የጉዳዩ አሳሳቢነት ተረድቶ የመጀመሪያ የህክምና እርዳታ ለማድረግ ይዋከባል።
አምቡላንሱ ከደቂቃዎች በኋላ ልምምድ ቦታው ላይ ሲደርስ የልብ ምቱ ስራ አቁሞ ነበር። ሆስፒታል እስኪደርስ ለሰባት ደቂቃ በዚህ ሁኔታ ውስጥ ቆየ።
ተጫዋቹ የገጠመው የልብ ህመም ነበር፤ ከዚህ ቀደም ችላ በማለቱ ህመሙ የከፋ ደረጃ ደርሶበት ከሞት አፋፍ አቅርቦታል፤ ነገር ግን በህክምና እርዳታ የልብ ምቱን የሚያስተካክል መሳሪያ ተገጥሞለት ሕይወቱ ወደ ቀድሞው ተመልሷል።

በዚህ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ያለፈው የቀድሞ ተጫዋች አሁን ኖርዌን በአሰልጣኝነት እየመራ የሚገኘው ስቴል ሶልባከን ነው። የ58 ዓመቱ አሰልጣኝ በተጫዋችነት ዘመኑ የተዋጣለት የአማካይ ስፍራ ተጫዋች ነበር።
በ33 ዓመቱ በጤናው ምክንያት ጫማ እስኪሰቅል ድረስ በተለይ በሀገሩ ክለቦች ኦልቡርግ እና ኮፐንሃገን ሲጫወት የዴኒሽ ሱፐር ሊግን አሸንፏል።
ለሀገሩ ኖርዌይ 16 ዓመታትን አገልግሎ 58 ጨዋታዎችን አከናውኗል። ዘጠኝ ግቦችንም ማስቆጠር የቻለ ድንቅ ተጫዋች ነበር።
በቆይታው ኖርዌይ ለዘንድሮ የዓለም ዋንጫ ከማለፏ በፊት ለመጨረሻ ጊዜ በተሳተፈችበት 1998ቱ የዓለም ዋንጫ ላይ የስብስቡ አካል ነበር።
ጫማ ከሰቀለ በኋላ ብዙም ሳይቆይ ወደ አሰልጣኝነቱ ሞያ ገባ ፤ የልጅነት ክለቡ በሆነው ሀምካም የጀመረው የአሰልጣኝነት ጉዞው በኩፐንሃገን በሁለት የተለያየ ጊዜ በጀርመኑ ኮሎኝ እና በእንግሊዙ ዎልቭስ እንዲሰራ አድርጎታል።

በኮፐንሃገን ቆይታው 13 ዋንጫዎችን ያሸነፈ ሲሆን፤ ከ2020 በኋላ ደግሞ የሀገሩን ብሔራዊ ቡድን እየመራ ይገኛል።
በ2022 የዓለም ዋንጫ እንዲሁም በ2024 የአውሮፓ ዋንጫ ቡድኑን ማሳለፍ ባይችልም የኖርዌይ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ከስቴል ሶልባከን ጋር መቀጠልን መርጧል። የፌዴሬሽኑ ውሳኔ ትክክል እንደነበር ብሔራዊ ቡድኑ ባለፉት ሁለት ዓመታት ያሳየው ብቃት ምስክር ነው።
ኖርዌይ ከ28 ዓመታት በኋላ ወደ ዓለም ዋንጫ የተመለሰችው በሶልባከን እየተመራች ነው። በማጣሪያው ጣልያን የነበረችበትን ምድብ ያደረገቻቸውን ስምንቱንም ጨዋታዎች አሸንፋ ነበር ወደ ታላቁ መድረክ የተመለሰችው።
አርሊንግ ሀላንድ ፣ ማርቲን ኦዴጋርድ ፣ አንቶኒዮ ኑሳ ፣ አሌክሳንደር ሶርሎዝ እና ሳንደር በርግ የመሳሰሉ ባለተሰጥኦዎችን የያዘችው ኖርዌይ በ23ኛው የዓለም ዋንጫ ኢራቅ እና ሴኔጋልን በማሸነፍ ወደ ጥሎ ማለፍ ዙር መሸጋገር ችላለች።

በተለይ ትናንት ለሊት ሴኔጋልን 3ለ2 ባሸነፉበት ጨዋታ አሰልጣኙ ስቴል ሶልባከን ስሜታዊ ሆኖ ታይቷል።
የብራዚላዊው ዋና ዳኛ ዊልተን ሳምፓዮ የጨዋታው መጠናቀቂያ ፊሽካ ሲሰማ ሮጦ ወደ ባለቤቱ ነበር ያቀናው።
እነዚያ ከሞት አፋፍ ደርሶ የተመለሰባቸውን አስቸጋሪ ጊዜያት በማሰብ ደስታውን ከባለቤቱ ጋር ለመጋራት ቢቻኮል አይገርምም።
ኖርዌይ ጉዞዋ በዚህ ብቻ ላያበቃ ይችላል። የስብስቡ ጥራት አዲስ ታሪክ መስራት የሚያስችል ነው።
ከዚያ አስቸጋሪ ጊዜ በኋላ ስኬታማ ጊዜን እያሳለፈ የሚገኘው አሰልጣኙ ስቴል ሶልባከን ታሪክም ደምቆ ይታያል።
በሸዋንግዛው ግርማ