AMN-ሰኔ 16/2018 ዓ.ም

ፖርቹጋል ኡዝቤኪስታንን 5ለ0 በማሸነፍ በ23ኛው የዓለም ዋንጫ የመጀመሪያ ድሏን አስመዝግባለች።
በሁስተን ስታዲየም በተደረገው ጨዋታ ክርስቲያኖ ሮናልዶ ሁለት ግቦችን አስቆጥሮ አዲስ ታሪክ አፅፏል።

የ41 ዓመቱ ተጫዋች በስድስት የዓለም ዋንጫዎች ግብ ያስቆጠረ የመጀመሪያው ተጫዋች ሆኗል። በአንድ ጨዋታ ሁለት ግብ ያስመዘገበ በዕድሜ ትልቁ ተጫዋችም ተብሏል።

በተሳተፈባቸው የዓለም ዋንጫዎች ያስቆጠራቸው ግቦች 10 አድርሷል። በዚህም ዘጠኝ ግቦች ያሉት ዩዞቢዮን በልጦ የሀገሩ የምንግዜም የዓለም ዋንጫ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ሆኗል።
የአልናስሩ ተጫዋች ለብሔራዊ ቡድኑ ያስቆጠራቸው ግቦች 145 ሲደርሱ ፤ በእግርኳስ ሕይወቱ ያስመዘገባቸው ግቦች ደግሞ 975 ሆነዋል።
የጨዋታውን ሌሎች ግቦች ኑኖ ሜንዴዝ ፣ ራፋኤል ሊያኦ እና ኔማቶቭ በራሱ ላይ አስቆጥረዋል።
በመጀመሪያ ጨዋታዋ ከዲ.ሪ ኮንጎ አቻ የተለያየችው ፖርቹጋል ምድብ 11ን በአራት ነጥብ መምራት ጀምራለች። በቀጣይ ከኮሎምቢያ ጋር ትጫወታለች።
በሸዋንግዛው ግርማ