AMN- ሰኔ 17/2018 ዓ.ም

በዩናይትድ ኪንግደም (እንግሊዝ) የተከሰተው ታይቶ የማይታወቅ የሙቀት ማዕበል ከፍተኛ ቀውስ እየፈጠረ ይገኛል።
ከሰዓታት በፊት በወጣ መረጃ መሠረት፣ በሀገሪቱ በደረሰው ከፍተኛ የሙቀት መጨመር ምክንያት በእንግሊዝና ዌልስ ውስጥ ከ1 ሺህ በላይ ትምህርት ቤቶች ለመዝጋት ተገደዋል።

በደቡባዊ እንግሊዝ የሙቀት መጠኑ እስከ 37 ዲግሪ ሴልሺየስ ይደርሳል ተብሎ ይጠበቃል።
ይሁን እንጂ የቢቢሲ የአየር ሁኔታ ባለሙያዎች እንደሚያስረዱት፣ በትክክል በሰውነት ላይ የሚሰማው የሙቀት መጠን ከተገለጸው ቁጥር በእጅጉ ሊበልጥ ይችላል።
የእንግሊዝ የአየር ንብረት ቢሮ (ሜት ኦፊስ) ከፍተኛውን የአደጋ ደረጃ የሚያመለክተውን “ቀይ ማስጠንቀቂያ” እስከ ነገ እኩለ ሌሊት ድረስ እንዲቆይ አራዝሞታል።

ይህ ማስጠንቀቂያ አሁን ላይ የደቡብ እንግሊዝ አካባቢዎችንም አካትቷል።
የሜት ኦፊስ ማስጠንቀቂያ ከፍተኛው የአደጋ ደረጃ ሲሆን፣ በሰዎች ሕይወት ላይ አደጋ ሊያስከትልና በትራንስፖርት እንቅስቃሴ ላይ መስተጓጎል ሊፈጥር የሚችል አስጊ ሁኔታ መኖሩን ያሳያል።
በደቡብ እና በምስራቅ እንግሊዝ የተከሰተውን አስከፊ ሙቀት ተከትሎ የባቡር ትራንስፖርት አገልግሎት መስተጓጎል ገጥሞታል።
የባቡር ተጓዦችም እጅግ አስፈላጊ ካልሆነ በስተቀር ማንኛውንም ዓይነት ጉዞ እንዲሰርዙ እየተመከሩ መሆኑን ቢቢሲ ዘግቧል።
በታምራት ቢሻው