AMN- ሰኔ 18/2018 ዓ.ም
የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ በሰጡት መግለጫ፤ ቻይና በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የሚመራው ብልጽግና ፓርቲ የኢትዮጵያን ጠቅላላ ምርጫ ድጋሚ በማሸነፉ የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፋለች።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጉዎ ጂያኩን፤ ቻይና የኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ስትራቴጂካዊ አጋር በመሆንዋ ሀገሪቱ ከብሔራዊ ነባራዊ ሁኔታዋ ጋር የሚስማማውን መንገድ እንድትከተል እንደምትደግፍ ገልጸው ፣ በሀገራዊ ልማትም የበለጠ ስኬት እንደምታስመዘግብ እንደምታምን ተናግረዋል።
ቻይና ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ግንኙነት በእጅጉ እንደምታከብር የገለጹት ጉዎ፤ የሁለቱ ሀገራት መሪዎች የደረሱባቸውን አስፈላጊ የጋራ ስምምነቶች እና የቻይና-አፍሪካ ትብብር ፎረም የቤጂንግ ጉባኤ ውጤቶችን ተግባራዊ ለማድረግ ከኢትዮጵያ ጋር ለመስራት ዝግጁ መሆኗን አክለዋል።
በሁለቱ ሃገራት መካከል በተለያዩ ዘርፎች የሚደረገውን ሁለንተናዊ ትብብር በማጠናከር ለሁለቱም ሕዝቦች የበለጠ ጥቅም ለማስገኘት እንዲሁም በቻይና እና አፍሪካ እንዲሁም በደቡባዊው የዓለም ክፍል መካከል ላለው የላቀ አንድነትና ትብብር የበኩሏን አስተዋፅኦ ለማበርከት እንደምትጥር መግለጻቸውን ዢንዋ ዘግቧል።