ሀገር የምትገነባው በትውልድ በመሆኑ፣ ተማሪዎች ውብና ለምለም ሀገርን ለመረከብ ዛሬውኑ ችግኞችን የመትከልና የመንከባከብ ልምድን ሊያዳብሩ ይገባል

AMN—ሀምሌ 1/2018 ዓ.ም

ሀገር የምትገነባው በትውልድ በመሆኑ፣ ታዳጊ ተማሪዎች ውብና ለምለም ሀገርን ለመረከብ ዛሬውኑ ችግኞችን የመትከልና የመንከባከብ ልምድን ሊያዳብሩ እንደሚገባ የአዲስ አበባ ከተማ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዘላለም ሙላቱ (ዶ/ር) ገለጹ።

‎የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ አመራሮች፣ ሠራተኞችና ባለድርሻ አካላት ጎሮ አካባቢ ችግኝ ተክለዋል።

‎”ተስፋን እንትከል” በሚል መሪ ሀሳብ እየተካሄደ በሚገኘው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ 20 ሺህ ችግኞችን በመትከል የድርሻውን እየተወጣ መሆኑን ገልጿል።

‎የቢሮው ኃላፊው ዘላለም ሙላቱ (ዶ/ር) የችግኝ ተከላ መርሃ ግብሩን ሲያስጀምሩ እንደተናገሩት፣ ሀገር የምትሠራው በትውልድ ስለሆነ ታዳጊ ተማሪዎች ያማረች ለምለም ሀገርን ለመረከብ ችግኞችን መትከልና መንከባከብን መለማመድ እንዳለባቸው አስገንዝበዋል፡፡

‎የቦሌ ክፍለ ከተማ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ አደፍርስ ኮራ በበኩላቸው በክፍለ ከተማው ዘንድሮ 1.8 ሚሊዮን ችግኞችን ለመትከል ታቅዶ እየተተገበረ መሆኑን አስታውቀዋል።

‎በችግኝ ተከላው ላይ ከቦሌ እና ከለሚኩራ ክፍለ ከተሞች የመጡ መምህራንና ተማሪዎች እንዲሁም ከሁሉም ክፍለ ከተማ በርካታ ቁጥር ያላቸው ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።

‎አረንጓዴ አሻራን ማኖር ልምላሜን ማስቀጠልና ሀገርን ማሻገር በመሆኑ እኛም ችግኞችን በመትከልና በመንከባከብ የዜግነት ድርሻችንን እንወጣለን ሲሉም ነው ተሳታፊዎች የገለጹት።

‎አዲስ አበባ ከተማ በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር 6 ሚሊዮን ችግኞችን የመትከል ግብን ለማሳካት እየሰራች ትገኛለች፡፡

‎በምትኩ ተሾመ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review