AMN ሃምሌ 1/2018 ዓ.ም

በአዲስ አበባ የቤት ኪራይ ጭማሪ ጣሪያ 11.5% ሆኖ ተወሰነ ፤ የውል እድሳት ምዝገባም ከዛሬ ሐምሌ 1 ጀምሮ እንደሚካሄድ የአዲስ አበባ የቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ አስታወቀ፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የዜጎችን የኑሮ ጫና ለመቀነስ እና በኪራይ ገበያው ላይ የሚስተዋሉ ህገ-ወጥና ዘፈቀዳዊ አሰራሮችን በዘላቂነት ለመግታት ታላቅ እርምጃ መውሰዱን ቀጥሏል።
ከዚህ ቀደም በወጣው የቤት ኪራይ ቁጥጥር አዋጅ መሠረት፣ ለ2019 በጀት ዓመት የሚተገበረው ፍትሐዊ የቤት ኪራይ ዓመታዊ ጭማሪ ጣሪያ 11.5% ሆኖ መጽደቁን የቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ አስታዉቋል።

ይህንን ተከትሎ በመላው ከተማዋ የሚገኙ የግል መኖሪያ ቤቶች የአከራይ-ተከራይ አዲስ የውል እድሳት ምዝገባ ከዛሬ ሐምሌ 1 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ በሁሉም ክፍለ ከተማ ቤቶች አስተዳደር ፅ/ቤት በይፋ መተግበር ይጀምራል።
ቢሮው እንዳመለከተው ፣ ይህ የዋጋ ማስተካከያ ውሳኔ በዘፈቀደ የተወሰነ ሳይሆን በከተማዋ ሰፊ ሳይንሳዊ ጥናት ተካሂዶ የነዋሪውን እውነተኛ የመክፈል አቅም ባገናዘበ መልኩ የተዘጋጀ ነው።
ይህ አሰራር በአንድ በኩል አከራዮች ወቅቱንና የኢኮኖሚ ሁኔታውን ያገናዘበ ፍትሐዊ ገቢ እንዲያገኙ የሚያረጋግጥ ሲሆን ፤ በሌላ በኩል ደግሞ ተከራዮች ከገቢያቸው ጋር የተመጣጠነ ኪራይ በመክፈል ከተደጋጋሚ መፈናቀልና ከስነ-ልቦና ስጋት ድነው የተረጋጋ ሕይወት እንዲመሩ ያደርጋል።
ውሳኔው በከተማዋ ያለውን የኑሮ ውድነት ጫና በከፍተኛ ደረጃ በመቀነስ ረገድ የጎላ ማህበራዊ ፣ ኢኮኖሚያዊ እና መልካም አስተዳደር ፋይዳዎች እንዳሉት ከአዲስ አበባ ቤቶች ልማት እና አስተዳደር ቢሮ ያገኘነዉ መረጃ ያመላክታል፡፡