የኑሮ ውድነትን ለማቃለል 18.2 ቢሊዮን ብር ድጎማ ተደርጓል- ከንቲባ አዳነች አቤቤ

You are currently viewing የኑሮ ውድነትን ለማቃለል 18.2 ቢሊዮን ብር ድጎማ ተደርጓል- ከንቲባ አዳነች አቤቤ

AMN-ሐምሌ 5/2018 ዓ.ም

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የኅብረተሰቡን የኑሮ ጫና ለማቃለልና የምርት አቅርቦትን ለማሳደግ ባከናወናቸው የተቀናጁ ስትራቴጂካዊ ሥራዎች አመርቂ ውጤቶች መመዝገባቸውን ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ፡፡

ከንቲባዋ ይህንን የገለጹት የከተማ አስተዳደሩን የ2018 ዓመታዊ የዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ለምክር ቤቱ ባቀረቡበት ወቅት ነው፡፡

እንደ ከንቲባዋ ማብራሪያ፣ ከተማ አስተዳደሩ በዝቅተኛ ገቢ የሚተዳደሩ የሕብረተሰብ ክፍሎችን ከኑሮ ጫና ለመታደግ 18.2 ቢሊዮን ብር በጀት መድጎም ተችሏል፡፡

ይህ ግዙፍ የድጎማ በጀት ለነዋሪው ቀጥተኛ እፎይታ ለሚሰጡ ዘርፎች የዋለ ሲሆን፤ በዋናነትም ለሕዝብ ትራንስፖርት፣ ለጤና መድህን፣ ለተማሪዎች ዩኒፎርምና ምገባ፣ ለዳቦ ምርት እንዲሁም ለሌሎች መሠረታዊ ምርቶች መዋሉ ተገልጿል፡፡

የምርት አቅርቦትን ለማጠናከር የተዘዋዋሪ ብድር ፈንድ ወደ 825 ሚሊዮን ብር በማሳደግ ለ11ዱም ዩኒየኖች ድጋፍ የተደረገ ሲሆን፣ የንግድ ኮርፖሬሽንም ከ5 ቢሊዮን ብር በላይ መነሻ ካፒታል ይዞ እንዲቋቋም መደረጉንም ከንቲባ አዳነች በሪፖርታቸው አብራርተዋል፡፡

በዚህም መሠረት በበጀት አመቱ 200 ሽሕ 434 ኩንታል ስኳር ለሕብረተሰቡ ተደራሽ የተደረገ ሲሆን፣ አስር ሚሊዮን አንድ መቶ ስልሳ ሰባትሽሕ ሁለት መቶ ሰባ አምስት/ሊትር የፓልም ዘይት በፍትሐዊነት እንዲሰራጭ መደሩም ተገልጿል፡፡

የምርት አቅርቦት ሰንሰለቱን በማሳጠር ነዋሪው ምርትን በቀጥታና በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያገኝ ሰፊ የመሠረተ-ልማት ግንባታ መከናወኑንም ከንቲባ አዳነች አቤቤ በሪፖርታቸው አብራርተዋል፡፡

በዚህም መሰረት በ15.9 ቢሊዮን ብር ወጪ 7 ዘመናዊ የግብርና ምርቶች መሸጫ ማዕከላት በአምስቱም የከተማዋ መግቢያዎች ተገንብተው ወደ ሥራ ገብተዋል ብለዋል፡፡

እነዚህ ማዕከላት 1 ሽሕ 247 የችርቻሮ፣ 88 የጅምላ መሸጫ ሱቆችን እንዲሁም 432 የምርት ማከማቻ መጋዘኖችን በውስጣቸው ያካተቱ መሆናቸውን ከንቲባዋ በሪፖርታቸው ገልጸዋል፡፡

የአማራጭ ገበያ ተደራሽነትን ለማስፋፋት ባለፉት አምስት ዓመታት የተጀመረው የቅዳሜና እሁድ ገበያ በአሁኑ ወቅት በአጠቃላይ ወደ 259 ከፍ እንዲል መደረጉንም ከንቲባ አዳነች በሪፖርታቸው ጠቁመዋል፡፡

የኑሮ ውድነትን ለመቀነስ በሌማት ትሩፋትና በከተማ ግብርና መርሃ-ግብር አማካኝነትም 1.2 ሚሊዮን ነዋሪዎች በቤተሰብ ደረጃ የዕለት ተዕለት የምግብ ፍጆታቸውን ራሳቸው እንዲያመርቱና ከወጪ እንዲታደጉ መደረጉን ከንቲባ አዳነች አቤቤ በሪፖርታቸው አብራርተዋል፡፡

በአስማረ መኮንን

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review