AMN-ሐምሌ5/2018 ዓ.ም
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ያከናወነው የከተማ ማደስና የኮሪደር ልማት ፕሮጀክት፣ ለዓመታት በአስከፊ የኑሮ ሁኔታ ውስጥ ይኖሩ የነበሩ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ የነዋሪዎችን ህይወት በዘላቂነት መለወጡን ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ፡፡
ከንቲባ አዳነች አቤቤ ለከተማው ምክር ቤት ባቀረቡት ሪፖርት ፣ የኮሪደር ልማቱ ዋና መነሻና መሠረት የነዋሪዎችን አስከፊ አኗኗር ማሻሻልና በጤናማ አካባቢ ለመኖር ምቹ የሆኑ ከባቢን መፍጠር መሆኑን አብራርተዋል፡፡

በተለይም የፍሳሽ ማስወገጃ መስመሮች መበላሸትና ያረጁ የጭቃ ቤቶች መውደቅ የዜጎችን ህይወት ፈታኝ አድርጎት እንደነበርና አሁን ላይ ግን ዜጎችን በከፍተኛ ጥንቃቄና በሚገባቸው ክብር የማስተናገድ ሰፊ ስራ ተሰርቷል፡፡
በዚህም ከ26 ሺህ በላይ መኖሪያ ቤቶች ተገንብተው የተሻሻሉ መኖሪያዎች ለመዲናዋ ነዋሪዎች መተላለፋቸውን ከንቲባ አዳነች ለምክር ቤቱ ባቀረቡት ሪፖርት ገልጸዋል፡፡
ከ40 ቢሊዮን ብር በላይ ካሳ ተከፍሎ 400 ሄክታር የሚጠጋ ምትክ መሬት መቅረቡንም ጠቅሰዋል።

በጥገኝነትና በደባልነት ህይወታቸውን ይገፉ ለነበሩ 3 ሺህ 700 በላይ ዜጎች አዲስ የመኖሪያ ቤት ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል ብለዋል፡፡
በኢኮኖሚ በኩልም የዜጎችን አቅም ለመደገፍ ከ4 ሺህ በላይ የንግድ ሼዶችና ወደ 5 ሺህ የሚጠጉ የመስሪያ ሱቆች ለነዋሪዎች መሰራጨታቸውን ከንቲባዋ በሪፖርታቸው አብራርተዋል፡፡
በታደሠ ሽፈራው