AMN-ሐምሌ5/2018 ዓ.ም
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የጸጥታ መዋቅር፣ የሰላም ሰራዊት እና ነዋሪዎች ባደረጉት የተቀናጀ ጥረት፣ ከተማዋ “የሰላም ከተማ” በሚል በምሳሌነት ተጠቃሽ መሆኗን ከንቲባ አዳነች አቤቤ አስታወቁ፡፡
ከንቲባዋ ይህን የተናገሩት የበጀት ዓመቱን አፈጻጸም አስመልክተው ለምክር ቤት አባላት በሰጡት ማብራሪያ ላይ ነው፡፡
ባለፉት አምስት ዓመታት በርካታ ሰላምን የማወክና ግጭት የማስነሳት እኩይ እቅዶች ቢያጋጥሙም፣ ህዝቡን በማሳተፍ በተሰራው ስራ አዲስ አበባ አንድም ኮሽታ ሳይሰማባት ፍጹም ሰላማዊ ሆና መዝለቋን ከንቲባዋ ጠቅሰዋል፡፡

ለዚህም ከ200 ሺህ በላይ የሠላም ሠራዊት እና ከ10 ሺህ በላይ የህዝብ ቅጥር ጥበቃ አባላትን በማደራጀት፣ በማሰልጠንና በማሰማራት የማይተካ ህዝባዊ ሚናቸውን እንዲወጡ መደረጉን አብራርተዋል፡፡ በዚህም በየጊዜው የሚነሱ የጸረ-ሰላም ኃይሎች ትንኮሳን ማምከን ተችሏል ብለዋል፡፡

በተጨማሪ የህግ የበላይነትን ከማረጋገጥ አኳያ፤ የህገ-ወጥ መሬት ወረራ እና የህገ-ወጥ ማስታወቂያ ፣ የህገ-ወጥ የጎዳና ንግድ፣ የህገ-ወጥ እንስሳት ዝውውርና እርድ፣ የህገ-ወጥ የመንገድ አጠቃቀም እና የህገ-ወጥ ግንባታ የቁጥጥር ስራዎች የህግ የበላይነትን በማስከበር የደንብ መተላለፎችን በዘላቂነት በመቀነስ የነዋሪውን ንብረትና መብት በማስከበር በኩል መሰረታዊ ለውጥ መመዝገቡን ከንቲባ አዳነች አቤቤ በሪፖርታቸው አመላክተዋል፡፡
በትዝታ መንግስቱ