የከተማዋን ገቢ የማሰባሰብ አቅም በ2013 በጀት አመት ከነበረበት 51 ቢሊየን ብር ወደ 350 ቢሊየን ማድረስ ተችሏል – ከንቲባ አዳነች አቤቤ

You are currently viewing የከተማዋን ገቢ የማሰባሰብ አቅም በ2013 በጀት አመት ከነበረበት 51 ቢሊየን ብር ወደ 350 ቢሊየን ማድረስ ተችሏል – ከንቲባ አዳነች አቤቤ
default

AMN- ሐምሌ 5/2018 ዓ.ም

በጀትን በአግባቡ ለዘላቂ ልማት በማዋል ረገድ የታዩ ለውጦች የከተማዋን የፋይናንስ አቅም በማጎልበት ለዜጎች የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት ያስቻሉ እና ጠንካራ የተጠያቂነት መሰረት የጣሉ ናቸው ሲሉ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 4ኛ መደበኛ ጉባኤውን እያካሄደ ይገኛል።

በጉባኤው ከንቲባ አዳነች አቤቤ፤ የአስተዳደራቸውን የ2018 በጀት ዓመት የዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ባቀረቡበት ወቅት እንዳስታወቁት፤ የገቢ መሰረትን በማስፋትና የሚሰበሰብ ገቢን ፍትሀዊነቱን በጠበቀ መልኩ እንዲሰበሰብ ከማድረግ አኳያ በሰፊው መሰራቱን ገልጸዋል፡፡

ባለፉት አምስት አመታት አገልግሎትን በማቀላጠፍ እና የአዲስ ግብር ከፋዮችን ቁጥር በማሳደግ የከተማዋን ገቢ በ2013 በጀት አመት ከነበረበት 51 ቢሊየን ብር በ2018 በጀት አመት ወደ 350 ቢሊየን ማድረስ ተችሏል ብለዋል።

የ2ዐ18 ገቢ አሰባሰብ ከ2017 በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ116.3 ቢሊየን ብር ወይም የ50 በመቶ እድገት ማሳየቱንም አስረድተዋል፡፡

በዚህ በጀት ዓመትም ከተማዋ በገቢ አሰባሰብና በጀትን በአግባቡ ለዘላቂ ልማት ከማዋል ጋር በተያያዘ ከአፍሪካ 6 ከተሞች ጋር በተሰራ ዝርዝር የምዘና ጥናት ቀዳሚ በመሆን ልምዷን ለማካፈል በቅታለች ብለዋል፡፡

በተጨማሪም የመንግስት ፋይናንስ አስተዳደር ስርዓትን በማሻሻል እና በኦዲት ግኝቶች ላይ ተገቢው ማስተካከያ የተደረገበት የገንዘብ መጠን ወደ 200 ሚሊየን ብር የፋይናንስ ተጠያቂነትን በማስፈን ማስመለስ ተችሏልም ነው ያሉት፡፡

እነዚህ ሁሉ ለውጦች የከተማዋን የፋይናንስ አቅም በማጎልበት ለዜጎች የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችልና ጠንካራ የተጠያቂነት መሰረት ጥለዋል ብለዋል፡፡

በዘንድሮ በጀት ዓመት ከተመደበው 360.07 ቢሊየን ብር ውስጥ ለዘላቂ ልማት 258.89 ቢሊየን ብር ወይም የበጀት ዓመቱ ጠቅላላ በጀት 71 በመቶ እድገት ተኮር ለሆኑ ዘላቂ ልማት እንዲመደብ በማድረግ 29 በመቶው ደግሞ ለመደበኛ ወጪ በስራ ላይ እየዋለ እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡

ለዘላቂ ልማትና ድህነት ቅነሳ የሚውለው ወጪ ድርሻ ከአምስት አመት በፊት ከነበረበት ከ47 በመቶ ወደ 71 በመቶ በማሳደግ የከተማዋን የወደፊት ብልጽግና መሰረት የሚጥል ጠንካራ የፋይናንስ አስተዳደር መዘርጋት ተችሏልም ብለዋል፡፡

የንብረት አስተዳደር ስርዓቱን በማዘመን የማንዋል አሰራርን በማስቀረት 699 የከተማ አስተዳደሩ ተቋማት የንብረት መረጃን ወደ ዘመናዊ የመረጃ ቋት እንዳስገቡም አብራርተዋል፡፡

እንዲሁም 6 ሺህ 815 የመንግስት ህንጻዎችን በሲስትም የማስገባት ስራ እንደተሰራም ከንቲባዋ ገልጸዋል፡፡

ባለፉት አምስት አመታት ለታላቁ የሕዳሴ ግድብ እስከተመረቀበት ጊዜ ድረስ ከ6.6 ቢሊየን ብር በላይ የድጋፍ ሃብት ማሰባሰብ እንደተቻለም ከንቲባዋ አንስተዋል፡፡

የሻምበል ምህረት

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review