AMN- ሐምሌ 6/2018 ዓ.ም

የከተማችን ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 4ኛ መደበኛ ጉባኤ በሁለተኛ ቀን ውሎው የአዲስ አበባ ከተማ ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት በከተማችን ተቋማት ላይ ያዘጋጀው የሥራ አፈጻጸም እና የኦዲት ሪፖርት ላይ ለምክር ቤት ቀርቦ ውይይት ተደርጎበት በሙሉ ድምፅ ፀድቋል ሲሉ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።

ከንቲባዋ በማሕበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት ፣ የኦዲት ሪፖርቱ የሸፈነው 107 የመንግስት ተቋማትን ሲሆን፣ የኦዲት አገልግሎት አይነቱ የፋይናንስ እና ህጋዊነት ኦዲት፣ ክዋኔ ኦዲት፣ የገቢ ኦዲት፣ የአካባቢ ኦዲትና የማጭበርበር ወይም ልዩ ኦዲት ናቸው ብለዋል።
የኦዲት ሥራው ዓለም አቀፍ የኦዲት ደረጃዎችን እና የኢትዮጵያ መንግሥት የሂሳብ አያያዝ ስርዓትን ተከትሎ የተከናወነ ነው ሲሉም ነው የገለጹት።
በዚሁ አግባብ ግኝቶቹ:-

ከንቲባ ጽ/ቤትን፣ ሥራና ክህሎት ቢሮንና ፕላንና ልማት ቢሮን ጨምሮ በ26 ተቋማት በተደረገው ኦዲት የተቀመጡትን የሂሳብ አያያዝ ደረጃዎችና አሰራሮችን ጠብቆ ምንም ነቀፌታ ያልተገኘባቸው፤ 49 ተቋማት ጉልህ ነቀፌታ ያልተገኘባቸው በመሆኑ በአጠቃላይ ኦዲት ከተደረጉት 70 % ሲሆኑ፤ 31 ተቋማት በተለይም የወረዳ ጽ/ቤቶችና ኮሌጆች የሂሳብ አያያዛቸው ችግር ያለበት መሆኑን የኦዲት ሪፖርት ግኝቱ ያሳያል ብለዋል።
በከተማችን የህዝብን ሃብት እና ንብረት እንዳይባክን፣ በአግባቡ ለታለመለት ዓላማ እንዲውል የኦዲት መስሪያ ቤቱ የክትትል ስራዎች በጥንካሬ የሚወሰድ ነው ሲሉም ገልጸዋል።

በኦዲት ግኝት መሰረት መታረም የሚገባቸውን እያረሙ፤ የአቅም ችግር ያለባቸው የፉይናንስ ሰራተኞችን በአቅም ግንባታ እንዲደገፉ ማድረግና የኦዲት ማጠናከር እንዲሁም ተቋማት ላይ ቀጣይ ክትትልና እርምት እየተወሰደባቸው የሚኬድ ይሆናል ብለዋል።
ከንቲባ አዳነች አቤቤ በመልዕክታቸው ዋና ኦዲት መስሪያ ቤት በአጠቃላይ የከተማዋ ገቢና ወጪ ጤናማ መሆኑን አረጋግጧል ሲሉ ገልጸዋል።