AMN- ሐምሌ 7/2018 ዓ.ም

የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ በመከላከያ ጠቅላይ መመሪያ ግቢ የ2018 ዓ.ም የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር በይፋ አሥጀምረዋል።
በመርሐ ግብሩ ማስጀመሪያ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ፤ የሀገር መከላከያ ሠራዊት የኢትዮጵያ ህዝብ አንድ አካል እንደመሆኑ መጠን የቀረበለትን ሀገራዊ ጥሪ በደስታ ተቀብሎ ከህዝብ ጋር በመሆን የችግኝ ተከላ መርሃ ግብሩን እንደሚያከናውን ገልፀዋል።

ሠራዊቱ ችግኝ መትከል ብቻ ሳይሆን የተተከሉትንም ተንከባክቦ ለፍሬ እንዲበቁ ለማድረግ ቁርጠኛ መሆኑን አረጋግጠዋል።
የመከላከያ ግብርና ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ቶማስ ቱት በበኩላቸው፤ በዘንድሮው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር በመከላከያ ሠራዊት ደረጃ በአጠቃላይ 20 ሚሊየን ችግኞችን ለመትከል እቅድ መያዙን አስታውቀዋል።

እቅዱ የአፈር መሸርሸርን ለመከላከልና የደን መመናመንን ለመግታት በሚያስችል መልኩ በተቀናጀና በታቀደ መንገድ በተለያዩ የልማት ስራዎች ላይ እየተተገበረ ይገኛልም ብለዋል።
መርሃ ግብሩ ከአገር ውስጥ የልማት ፋይዳው ባሻገር ዓለም አቀፍ ትኩረትን መሳብ መቻሉም ተገልጿል።

የመከላከያ ሰራዊቱ ለአገር ሰላምና ዕድገት ሲል ውድ ህይወቱን እየገበረ ከመሆኑም ባሻገር በጉልበቱም ሆነ በገንዘቡ አገራዊ የልማት ጥሪዎችን በግንባር ቀደምትነት እየደገፈ ይገኛልም ብለዋል፡፡
ይህ በዛሬው እለት በይፋ የተጀመረው የችግኝ ተከላ ንቅናቄ በሁሉም የሰራዊት ክፍሎችና እዞች ውስጥ እስከ መጪው ነሐሴ ወር መጨረሻ ድረስ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ከመከላከያ ሰራዊት ማህበራዊ ትስስር ገጽ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡