የመጀመሪያው የአፍሪካ ማህበራዊ ሚዲያ ተጽዕኖ ፈጣሪዎች ጉባኤ ነገ እና ከነገ በስቲያ በአዲስ አበባ ይካሄዳል

You are currently viewing የመጀመሪያው የአፍሪካ ማህበራዊ ሚዲያ ተጽዕኖ ፈጣሪዎች ጉባኤ ነገ እና ከነገ በስቲያ በአዲስ አበባ ይካሄዳል

AMN- ሚያዝያ 28/2018 ዓ.ም

የአፍሪካን እውነተኛ ገጽታ ለዓለም ለማስተዋወቅና የዲጂታል ትርክቱን በባለቤትነት ለመምራት ያለመው የመጀመሪያው የአፍሪካ ማህበራዊ ሚዲያ ተጽዕኖ ፈጣሪዎች ጉባኤ (ASMIS 2026) በአዲስ አበባ ዓድዋ ድል መታሰቢያ ነገ እና ከነገ በስቲያ ይካሄዳል።

በጉባኤው ላይ ከ30 የአፍሪካ ሀገራት የተውጣጡ 61 ተጽዕኖ ፈጣሪዎችን የሰበሰበ ሲሆን፣ እነዚህ ግለሰቦች በድምሩ 321 ሚሊየን የሚጠጋ ተከታይ አላቸው።

ከእነዚህም በተጨማሪ 150 ሚሊየን ተከታዮች ያላቸው 120 ኢትዮጵያውያን የይዘት ፈጣሪዎች በጋራ በመሰባሰብ፣ በአህጉሪቱ ዲፕሎማሲያዊ ማዕከል አዲስ አበባ ላይ አዲስ የዲጂታል ታሪክ ለመጻፍ ተዘጋጅተዋል።

ለዚህ ደማቅ መድረክ ታዋቂው ኡጋንዳዊ የቲክቶክ ኮከብ ሳድ ሶዚ (ቴንጌ ቴንጌ) አዲስ አበባ የገባ ሲሆን፣ ሌሎች የአህጉሪቱ የዲጂታል ድምጾችም ደርስዋል፡፡

ከኡጋንዳዋ ካዚንጋ መንደር በመነሳት በደማቅ የዳንስ ትርኢቶቹ ዓለም አቀፍ ዝናን ያተረፈው ቴንጌ ቴንጌ፣ ዛሬ ላይ ከመዝናኛ ባለፈ የሕፃናት መብት ተሟጋችና ድምጽ ሆኖ ብቅ ብሏል።

የእርሱ በጉባኤው ላይ መገኘት፣ አፍሪካውያን የይዘት ፈጣሪዎች ከግል ዝና ባለፈ ለአህጉራዊ ልማትና ለዲፕሎማሲያዊ ተፅዕኖ ያላቸውን ሚና ማሳያ ተደርጎ ተወስዷል።

የጉባኤው አዘጋጆች እንደገለጹት፣ መድረኩ የይዘት ፈጣሪዎችን እንደ ተራ አዝናኞች ሳይሆን እንደ ባህል አምባሳደሮችና የለውጥ ወኪሎች እውቅና የሚሰጥ ነው።

ተፅዕኖ ፈጣሪዎቹ ስለ አፍሪካ የሚነገሩ የተሳሳቱ ትርክቶችን በመቀየር፣ ቱሪዝምን በማስፋፋትና የውጭ ኢንቨስትመንትን በመሳብ ረገድ ዋና ተዋናይ እንዲሆኑ ጥሪ ቀርቧል።

ለቴንጌ ቴንጌ እና ለጓደኞቹ ይህ ጉባኤ ከታዋቂነት በዘለለ ትልቅ ኃላፊነት ያለበት መድረክ ነው።

ፈጠራን ከማህበራዊ ተፅዕኖ ጋር በማጣመር፣ የአፍሪካን ብዝሃነት፣ ጥንካሬና የወደፊት ተስፋ በራሳቸው በአፍሪካውያን አንደበት ለዓለም ለማሳየት ትልቅ ዕድል ይፈጥራል ተብሎ እንደሚጠበቅ ኢዜአ ዘግቧል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review