ከጉባዔው የምንጠብቃቸው ውጤቶች የሀገራችንን ዕጣ ፈንታ የሚወስኑ ናቸው – መስፍን አርዓያ (ፕ/ር)

You are currently viewing ከጉባዔው የምንጠብቃቸው ውጤቶች የሀገራችንን ዕጣ ፈንታ የሚወስኑ ናቸው – መስፍን አርዓያ (ፕ/ር)

AMN – ሐምሌ 8/2018 ዓ.ም

በዚህ ታሪካዊ ሀገራዊ ምክክር ጉባዔ የምንጠብቃቸው ውጤቶች ታላላቅ የሀገራችንን የወደፊት ዕጣ ፈንታ የሚወስኑ ናቸው ሲሉ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር መስፍን አርዓያ (ፕ/ር) ገለጹ፡፡

በሀገራችን ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክር ጉባዔ በአዲስ ኮንቬንሽን ሴንተር መካሄድ ጀምሯል፡፡

ጉባዔው እየተካሄደ ያለው በምክክር የምትጸና ሀገር በሚል መሪ ሐሳብ ነው፡፡

በዚሁ ወቅትም መስፍን አርዓያ (ፕ/ር) ባደረጉት ንግግር፤ የሐሳብ ልዩነት ውበትና የዴሞክራሲ አካል ቢሆንም ችግሩ ልዩነቶችን በውይይት ፈንታ በኃይልና በኩርፊያ ለመፍታት መሞከሩ መሆኑን አስገንዝበዋል።

የሀገሪቱን ሥር የሰደዱ የፖለቲካና የማኀበራዊ ችግሮች በጊዜያዊ ማስታገሻ መፍታት እንደማይቻል በመግለጽ፤ አስተማማኝ መንገድ የሆነው አካታችና ሳይንሳዊ ሀገራዊ ምክክር መሆኑን በአጽንዖት አንስተዋል።

ግልጽ የአሠራር ሥርዓቶችን የመዘርጋት፣ ተሳታፊዎችን በገለልተኝነት የመለየት እና ከመላው ሀገሪቱ አጀንዳዎችን በምሁራን ታግዞ የማሰባሰብና የመቅረጽ ሥራዎች በጥንቃቄ መከናወናቸውንም አረጋግጠዋል።

የጉባዔው ተሳታፊዎች ከቡድንና ከግል ፍላጎት ወጥቶ ታላቋን ኢትዮጵያን ማዕከል በማድረግ በቀናነት፣ በሆደ-ሰፊነትና በሀቀኝነት እንዲመክርም ጥሪ አቅርበዋል።

በጉባዔው ላይ ከመላው ኢትዮጵያ የተውጣጡ ከ4 ሺህ በላይ ተሳፊዎች ተገኝተዋል፡፡

በታምራት ቢሻው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review