ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ በጄኔራል ዳግቪን አንደርሰን ከተመራ የአፍሪኮም ልዑክ ጋር ተወያዩ

AMN- ሐምሌ 20/2018 ዓ.ም

የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ በአፍሪካ የአሜሪካ ዕዝ (አፍሪኮም) አዛዥ ጀነራል ዳግቪን አንደርሰን ጋር ተወያይተዋል፡፡

በውይይታቸውም በሁለቱ ሀገራት መካከል ባለው የመከላከያ ትብብር፣ በቀጣናዊ ደህንነት እና በጋራ የሚከናወኑ የወደፊት የትብብር መስኮች ላይ መክረዋል፡፡

በአፍሪካ የአሜሪካ ዕዝ (አፍሪኮም) አዛዥ ጀነራል ዳግቪን አንደርሰን ውይይቱን አስመልክተው በሰጡት ማብራሪያ፤ ከኢትዮጵያ ጋር ያለው የመከላከያ ትብብር በተለያዩ ዘርፎች እየተጠናከረ መምጣቱን ገልጸው ይህም በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የረጅም ጊዜ የመከላከያ አጋርነትና የጋራ ቁርጠኝነት የሚያንጸባርቅ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በውይይቱ ወቅት የትብብር መስኮችን ማስፋት፣ በሶማሊያ አልሸባብንና አይኤስ አይኤስን ጨምሮ በሽብርተኝነት ላይ የሚደረገውን ትግል ማጠናከር እንዲሁም ወደፊት ያሉ የትብብር ዕድሎችን መለየት ዋና የውይይቱ አጀንዳዎች እንደነበሩ ገልጸዋል።

ለቀጣናው ሰላምና መረጋጋት ኢትዮጵያ እያበረከተች ያለችውን አስተዋፅኦ ያደነቁት ጀነራል መኮንኑ፤ ከኢትዮጵያ ጋር በጋራ የአፍሪካ የሎጂስቲክስና የኮሙኒኬሽን ሲምፖዚየምን ማዘጋጀት መቻላቸው በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው የመከላከያ ትብብር የደረሰበትን ከፍተኛ ደረጃ የሚያሳይ መሆኑን ጠቁመዋል።

የሁለቱ ወዳጅ ሀገራት ግንኙነት ከጋራ ወታደራዊ ተልዕኮዎች ባሻገር ዘላቂና ዘመናዊ የመከላከያ አቅምን በመገንባት ላይ ያተኮረ ሲሆን በአህጉሪቱ ያሉ የደህንነት ተግዳሮቶችን በጋራ ለመፍታት ያለውን ቁርጠኝነት እንደሚያሳይም ጠቁመዋል።

የጉብኝታቸው ዋና ዓላማ ከኢትዮጵያ ብሄራዊ መከላከያ ሠራዊት ጋር በመተባበር የአፍሪካ የሎጂስቲክስና የኮሙኒኬሽን ሲምፖዚየምን ማካሄድ መሆኑን ገልጸው ሲምፖዚየሙ ልምድ ለመለዋወጥ፣ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ለማስተዋወቅ፣ ከንግድ ዘርፉ ጋር ትብብርን ለማሳደግና የአፍሪካ የመከላከያ ተቋማትን አቅም ለማጠናከር ጠቃሚ መድረክ መሆኑን አስታውቀዋል።

በተጨማሪም ኢትዮጵያ የአህጉሪቱን ሀገራት በአንድ መድረክ በማሰባሰብ የጋራ የደህንነት ችግሮችን ለመፍታት ያላትን የአመራር ሚና እያሳየች መሆኑን ገልጸዋል።

የመከላከያ የውጭ ግንኙነትና ወታደራዊ ትብብር ዋና ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ሜጀር ጄኔራል ተሾመ ገመቹ በበኩላቸው፣ ውይይቱ ፍሬያማ እንደነበርና በኢትዮጵያና በአሜሪካ መካከል ያለውን የረጅም ጊዜ ወዳጅነትና የመከላከያ ትብብር የበለጠ የሚያጠናክር መሆኑን ተናግረዋል።

በውይይቱ በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ኤርቪን ማሲንጋን ጨምሮ የሁለቱ አገራት ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖች መሳተፋቸውን ከመከላከያ ሰራዊት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review