AMN- ነሐሴ 13/2018 ዓ.ም
የቆዳ አለርጂ ፣ለቆዳችን ከምንጠቀማቸው ነገሮች ጋር ሳይስማማ ሲቀር የሚከሰት የጤና ችግር መሆኑን በአለርት አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የቆዳና የአባለዘር በሽታዎች ስፔሻሊስት ሀኪም ዶክተር አቡናስር ሐምዛ ከኤ ኤም ኤን ጋር በነበራቸው ቆይታ ገልጸዋል።
የቆዳ አለርጂ መንስኤዎች
አለርጂ በተለያዩ ነገሮች ሊከሰት የሚችል ሲሆን ከቆዳ ጋር በተያያዘ በብዛት የሚቀቡ ቅባቶች፣ መዋቢያዎች ፣ ጌጣ ጌጦች፣ የፀጉር ቀለም እና ፈሳሽ ሳሙናዎች፣ ኬሚካሎች እና የቤት ውስጥ ማጽጃዎች ይከሰታል፡፡
ዋና ዋና የህመም ምልክቶች በሰውነት ላይ የሚወጣ ሽፍታና መቅላት፣ ከፍተኛ ማሳከክ እና የቆዳ መቆጣት፣ አንዳንዴም ሙሉ አካልን ሊያዳርስ የሚችል መገለጫዎች፣ እንደ ሁኔታው የትንፋሽ ውጥረት ምልክቶች ሊታወቅ ይችላል ብለዋል፡፡

ለመጀመሪያ ጊዜ ለኬሚካሉ ስንጋለጥ ምልክቱ ከ10 ቀን እስከ 2 ሳምንት ሊወስድ ይችላል። ነገር ግን ለሁለተኛ ጊዜ ከተጋለጥን በ48 እስከ 72 ሰዓታት ውስጥ ቆዳችን ተቆጥቶ ምልክቶቹን ማሳየት ይጀምራል።
የፀጉር ባለሙያዎች፣ የቤት ውስጥ ሠራተኞች እና የምግብ ቤት ሠራተኞች እንዲሁም ከእቃ ማጠቢያ ሳሙናዎች ጋር በብዛት የሚገናኙ አካላት ለዚህ ችግር በከፍተኛ ሁኔታ ተጋላጭ መሆናቸውንም ዶክተር አቡናስር ሐምዛ አንስተዋል፡፡
መፍትሄዎች እና የጥንቃቄ እርምጃዎች
አለርጂው የሚያመጣውን ነገር ለይቶ ማወቅና ማስወገድ፣ ቆዳችንን የሚያቆስለውን ወይም አለርጂ የሚፈጥርብንን ነገር ማራቅ።
አለርጂው አንዴ ከተከሰተ ሐኪም ዘንድ በመቅረብ የሚቀቡ ወይም የሚዋጡ መድኃኒቶችን በአግባቡ መጠቀም ተገቢ መሆኑን የሚገልጹት ዶክተሩ፤ ሐኪም ያዘዘውን መድኃኒት “ለጥቂት ቀናት ተሻሽሎልኛል” ብሎ በግማሽ አለማቋረጥ፣ በታዘዘው ልክ ሙሉ ጊዜውን መጠቀም (ካልተጠናቀቀ የማገርሸት ወይንም ተባብሶ የመመለስ ዕድል አለው)።
ቅባቶችን መጠቀም
ለተጋላጭ ሙያተኞች እንደ ቫዝሊን፣ ፓራፊን እና ግሊሰሪን የመሳሰሉ ቅባቶችን እየተጠቀሙ ለጉዳት እንዳይጋለጡ መጠንቀቅ ይቻላል ብለዋል።
በፍሬሕይወት ብርሃኑ