AMN – ነሐሴ 15/2018 ዓ.ም

በአሜሪካ፣ በእስያ እና በአውሮፓ እንደሚገኙ ታዋቂ የቱሪስት መዳረሻዎች ሁሉ አዲስ አበባም የበርካታ ዓለም አቀፍ ጎብኚዎች የጉዞ ህልም እየሆነች ትገኛለች።

ለዘመናት በአፍሪካ የዲፕሎማሲ ማዕከልነቷ የምትታወቀው አዲስ አበባ አሁን ላይ በፈጣን የዕድገት እንቅስቃሴዋ፣ በግዙፍ የልማት ሥራዎቿና በዘመናዊ የኮሪደር ልማት ፕሮጀክቶች አማካኝነት ይበልጥ ተመራጭና ማራኪ የቱሪስት መዳረሻ ወደመሆን ተሸጋግራለች።

አዲስ አበባ የአፍሪካ ኅብረት እና የተባበሩት መንግሥታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽንን ጨምሮ የበርካታ ዓለም አቀፍ ተቋማት መቀመጫ ናት።
ይህም ከተማዋን የከፍተኛ ዲፕሎማሲያዊ ውይይቶችና ዓለም አቀፍ ጉባዔዎች ማዕከል ከማድረጉም ባሻገር፤ በየዓመቱ በሺዎች የሚቆጠሩ ዓለም አቀፍ ተሳታፊዎችን በማስተናገድ ቀዳሚ የኮንፈረንስ ቱሪዝም መዳረሻ እንድትሆን አድርጓታል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በከተማዋ በተሳካ ሁኔታ እየተተገበሩ ያሉት ስልታዊ የኮሪደር ልማት ሥራዎች የአዲስ አበባን ገጽታ በአዲስ መልክ ቀይረውታል። ሰፊ የእግረኛና የብስክሌት መንገዶች፣ እንዲሁም አዳዲስ አረንጓዴ መናፈሻዎች ከተማዋን ለዓይን ማራኪ አድርገዋታል።
እነዚህ ዘመናዊ መሠረተ ልማቶች የነዋሪዎችን የኑሮ ጥራት ከማሻሻል አልፈው፤ የውጭ ቱሪስቶች ከተማዋን በእግራቸው እየተዘዋወሩ በነፃነትና በደኅንነት እንዲጎበኙ የሚያስችል ምቹ ከባቢ ፈጥረዋል።

እንደ ብሔራዊ ቤተ-መንግስት ሙዚየምና የአንድነት ፓርክ ያሉ ሥፍራዎች የኢትዮጵያን የበለጸገ ታሪክና ቅርስ በድምቀት ሲያንጸባርቁ፤ እንደ ሳይንስ ሙዚየምና እንጦጦ ፓርክ ያሉት አዳዲስ መዳረሻዎች ደግሞ የከተማዋን ዘመናዊ ዕይታ ያሳያሉ።
ከዚህ ጎን ለጎን የተገነቡት ዘመናዊ የንግድ ማዕከላት፣ ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ ሆቴሎችና የጥበብ ሥፍራዎች የቱሪዝም ገቢን ከማሳደግ ባሻገር ከተማዋን የባህል ልውውጥ ማዕከል አድርገዋታል።

የቱሪዝም ዕድገቱን ይበልጥ ለማሳለጥ አዲስ አበባ የዲጂታል ቴክኖሎጂን ወደ ዘርፉ በማስገባት ፈጣን ለውጥ እያሳየች ነው።
እንግዶች ወደ ከተማዋ ሲገቡ የትራንስፖርት፣ የሆቴል ምዝገባና የቱሪስት መረጃዎችን በቀላሉ እንዲያገኙ የሚያስችሉ ዘመናዊ ሥርዓቶች መዘረጋታቸው የቱሪስቶችን ቆይታ ይበልጥ ምቹና ቀልጣፋ አድርጎታል።
ከነዚህ ሁሉ መሠረተ ልማቶችና አዳዲስ ገጽታዎች ባሻገር ግን፣ የአዲስ አበባ መለያ የሆነው ታላቁ እሴት የሕዝቧ ሞቅ ያለ አቀባበልና እንክብካቤ ነው።
ኢትዮጵያውያን ለዕንግዳ ያላቸው አክብሮትና የእንግዳ ተቀባይነት ባህል የቱሪስቶችን ልብ የሚስብ ነው።
በወርቅነህ አቢዮ