የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ አፍሪካ በራሷ እጣ ፈንታዋን የመወሰን ጉዞ ማሳያ ነው- ኡሁሩ ኬንያታ

AMN- ነሐሴ 16/2018 ዓ ም

ኢትዮጵያ ያካሄደችው ስኬታማ ሀገራዊ ምክክር አፍሪካ የራሷን ጉዳይ በራሷ የመወሰን አቅም ያመላከተ መሆኑን የቀድሞው የኬንያ ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ገለጹ።

ኡሁሩ ኬንያታ ይህን ያሉት ከመላው ሀገሪቱ በሕዝቡ በተወከሉ 4 ሺህ ተመካካሪዎች መካከል ከሀምሌ 8/2018 ዓ.ም ጀምሮ ሲካሄድ የቆየው የሀገራዊ ምክክር ጉባኤ የመዝጊያ ስነ ስርዓት ላይ ባደረጉት ንግግር ነው።

ኬንያታ አክለውም፣ አፍሪካ ታላላቅ ትልሞችን የማለምና የራሷን የወደፊት እጣ ፈንታ የመወሰን አቅም እንዳላት ገልጸው፣ ለዚህም ይሄ ስኬታማ የምክክር ሒደት አንዱ ማሳያ መሆኑን አብራርተዋል።

አዲስ አበባ የኢትዮጵያ መዲና ብቻ ሳትሆን የአፍሪካ ህያው ከተማ መሆንዋንና አፍሪካ መፍትሄዎችን ስትፈልግ ዞር ብላ የምታያት ዋና ማዕከል መሆኗን የጠቆሙት ኡሁሩ ኬንያታ፤ ኢትዮጵያውያን እንደ ወርቅ በእሳት ተፈትነው ያለፉ ጠንካራና በችግሮች የማይበገሩ በመሆናቸው ለአፍሪካውያን ምሳሌ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የቆዩ የታሪክ ቁርሾዎችን ለመፍታት ያዘጋጀው ጉባኤ ብዝሃ ድምጾች የተሰሙበት፣ ከሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች የተሳተፉበት አካታች እና የሀገር ፍቅር ስሜት የተንጸባረቀበት መሆኑንም አብራርተዋል።

ኢትዮጵያዊያን በርካታ ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ ቅርሶች እንዳላቸው የገለጹት ኬንያታ፣ በህዝቦች መካከልም የቆየ የወዳጅነት ትስስር መኖሩን አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ታሪክ የጽናት እና የአይበገሬነት ምልክት መሆኑን ያነሱት ኬንያታ፤ የአድዋ ድል ለአፍሪካ ነጻነት ትግል ትልቅ መሰረት የጣለ፣ የአህጉሩ ኩራት መሆኑን፣ ኢትዮጵያም የሊግ ኦፍ ኔሽን መስራች፣ የአፍሪካ ህብረት መቀመጫና የጥንታዊ ስልጣኔ መገለጫ መሆኗን አብራርተዋል ።

በመጨረሻም የምክክር ሒደቱ በስኬት በመጠናቀቁ ለመላው ኢትዮጵያዊያን የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

በአስማረ መኮንን

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review