በሽታን ቀድሞ የመከላከል እና የጤና ተቋማትን ማስፋት የኢትዮጵያ ተሞክሮ ለሌሎች አገራት በልምድ ሊወሰድ ይገባል – ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ

AMN – ነሐሴ 19/2018 ዓ.ም

የኢትዮጵያ በሽታን ቀድሞ የመከላከል እና የጤና ተቋማትን የማስፋት ተሞክሮ በሌሎች አገራት በልምድ መልክ ሊቀመር የሚገባው መሆኑን የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ታየ አጽቀ ሥላሴ ተናገሩ።

76ኛው የዓለም ጤና ድርጅት የአፍሪካ ቀጣናዊ ኮሚቴ ስብሰባ በአዲስ አበባ በመካሄድ ላይ ይገኛል።

ፕሬዚዳንት ታየ አጽቀሥላሴ በጉባኤው ላይ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ በሽታን ቀድሞ በመከላከል እና ለድንገተኛ ወረርሽኞች ፈጣን ምላሽ የመስጠት አስተማማኝ አቅም ገንብታለች። በሌላ በኩል የጤና ተቋማትን በመላ አገሪቱ ማስፋት፣ ደረጃቸውን ማሻሻል እና የማዘመን ሥራ ላይ አበክሮ መሠራቱንም ጠቁመዋል።

አፍሪካን የጤና ሥርዓት ለማዘመን እና የተደራሽነት ሥርዓቱን እውን ለማድረግ የአገራቱ ትብብር እና ከጥገኝነት የተላቀቀ የጤና ሥርዓት ትልቁን ስፍራ እንደሚይዝም አጽንኦት ሰጥተዋል።

ኢትዮጵያ የጤና ቱሪዝም መዳረሻ ለመሆን፣ የሕዝቦቿን ጤንነት እና ደህንነት ለማስጠበቅ የመድኃኒት አቅርቦትና ምርታማነትን ማዘመን፣ የአገልግሎት አሰጣጥ ሥርዓትን ማስተካከል እና በጤና ዘርፍ ብቁ ባለሙያዎችን ለማብዛት በትኩረት እየሠራች መሆኑንም ገልጸዋል።

የተፈጥሮ ሚዛንን ለመጠበቅ አገሪቱ ባለፉት ዓመታት የተገበረችው የአረንጓዴ አሻራ ንቅናቄ እንዲሁም የከተሞችን ደረጃ በማሻሻል እና በማዘመን የዜጎችን አኗኗር ለማሻሻል በኩል የሚታዩ ሥራዎች መሠራታቸውን አንስተው፣ አዲስ አበባ ከተማን በአብነት ጠቅሰዋል።

በመጨረሻም ጉባኤው ለፖሊሲ አውጪዎች፣ ለዘርፉ ባለሙያዎች እና ለሀገራቱ መንግሥታት የትናንት የጤና ዘርፍ ክፍተቶችን በውል በመለየት ለነገ የተሻለ የጤና ሥርዓት ለመንደፍ ትልቅ ዕድል እንደሚፈጥር ፕሬዚዳንቱ አመላክተዋል።

በተመስገን ይመር

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review