የነቢዩን በጎ እሴቶች፣ ፍቅርና አስተምህሮዎች በዕለታዊ ሕይወት ውስጥ በተግባር መተርጎም ይገባል

AMN- ነሐሴ 19/2018 ዓ.ም

የነቢዩ ሙሐመድ የልደት በዓል (መውሊድ) የአንድ ቀን የአከባበር ሥነ-ሥርዓት ብቻ ሆኖ ማለፍ የለበትም። ይልቁንም የነቢዩን በጎ እሴቶች፣ ፍቅርና አስተምህሮዎች በዕለታዊ ሕይወት ውስጥ በተግባር በመተርጎም፣ በፍትሐዊነትና በደግነት የታነፀ የተመሰገነ ትውልድ ለመገንባት የሚያስችል ጠንካራ መሠረት ሊሆን እንደሚገባ የእስልምና ሐይማኖት መምህር ኡስታዝ ፉአድ አብዱ ገልጸዋል፡፡

ኡስታዝ ፉአድ አክለውም ለትውልድ የምናበረክተው ትልቁ ስጦታ ቁሳዊ ሀብት ብቻ ባለመሆኑ፣ እውነትን የሚናገር ልብ፣ የሌላውን መብት የሚያከብር ሕሊና፣ ሥልጣንን በትሕትና የሚጠቀም አእምሮና ለፍትሕ የሚቆም ዜጋ መፍጠር እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

ይህ የትውልድ ግንባታ ሂደት ከቤተሰብ ተጀምሮ በትምህርት፣ በሃይማኖትና በማኅበራዊ ተቋማት ድጋፍ የሚጎለብት መሆኑንም ጠቁመዋል።

የእስልምና እምነት መምህር ኡስታዝ ፉአድ እንደሚገልጹት፣ ነቢዩ ሙሐመድ ከነቢይነት ጥሪያቸው በፊትም ቢሆን በማኅበረሰቡ ዘንድ ‘አል-አሚን’ (ታማኙ) ተብለው ይጠሩ ነበር። ወደ መዲና በተሰደዱበት (ሂጅራ) ወቅት እንኳን ሊገድሏቸው በከበቧቸው ሰዎች የተቀመጡ አደራዎችንና ንብረቶችን እንዲመልሱ ለአጎታቸው ልጅ ለኢማም አሊይ አደራ ሰጥተው መውጣታቸው የዚህ ታማኝነት ቁልፍ ማሳያ ነው።

ስለሆነም በዛሬው የቴክኖሎጂና የቁሳዊ ፍላጎት ዘመን ማኅበረሰቡ ከሁሉ በላይ ቅንነት፣ እውነተኝነት፣ ፍትሕ፣ ትሕትናና ርኅራኄ ያስፈልገዋል።

እውነተኝነት በቃል ብቻ ሳይሆን በሐሳብ፣ በንግግርና በተግባር መጣጣም እንደሆነ የጠቀሱት ኡስታዝ ፉአድ፣ የዚህ እሴት ዘመናዊ መገለጫዎች በትምህርት ቤት ፈተናን አለማጭበርበር፣ በሥራ ቦታ የሌሎችን መብት አለመጋፋት፣ በንግድ ደንበኛን አለማታለል፣ ለሕዝብ ሀብት ታማኝ መሆን እና በዲጂታል ዓለም የሐሰት መረጃ አለማሰራጨት እንደሆኑ አብራርተዋል። በተጨማሪም ትሕትና ሌሎችን አለመናቅና ስህተትን አምኖ መቀበል ሲሆን፣ ፍትሕ ደግሞ የሚወዱትን ብቻ ሳይሆን የሁሉንም ሰው መብት በእኩል ማከብር እንደሆነ ገልጿል።

ስለሆነም መውሊድ ሲከበር “ነቢዩን ምን ያህል አስታወስን?” ከሚለው ጥያቄ ባሻገር፣ ከአርአያነታቸው የተማርናቸውን እሴቶች በየዕለቱ ተግባራዊ በማድረግ ከ“እኔ” ወደ “እኛ” የሚሸጋገር የሥነ-ምግባር ጉዞ ማድረግ ያስፈልጋል።

የመውሊድ በዓል በዓመት አንድ ጊዜ የሚከበር የቀን ሥነ-ሥርዓት ብቻ ሳይሆን፣ እነዚህን ታላላቅ እሴቶች በየዕለቱ መኖርና ማኅበረሰቡን ከውስጣዊ የሥነ-ምግባር ውድቀትና ከስብዕና ብልሹነት መጠበቅ እንደሚገባ ኡስታዝ ፉአድ መልዕልቱን አስተላልፏል።

በቶለሳ መብራቴ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review