AMN- ነሐሴ 19/2018 ዓ.ም
በከተማችን ላይ ከሚታየው ለውጥ ሁሉ የሚልቀው በለነገዋ ሴቶች ላይ እያየን ያለው ለውጥ ነው ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ፡፡
ከንቲባ አዳነች አቤቤ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልእክት፤ የልጆች ኢንቨስትመንት ፈንድ ፋውንዴሽን (CIFF) መስራች እና የቦርድ ሃላፊ ክሪስ ሆን እና ቡድናቸውን ለነገዋ የሴቶች የተሃድሶና ክህሎት ማበልፀጊያ ማዕከልን አስጎብኝተናል ብለዋል፡፡
ለነገዋ ጅማሮው በተለያዩ ማህበራዊ ችግር ውስጥ ያሉ ሴቶች እህቶቻችን ተስፋና እድላቸው እዲለመልም፣ ክብራቸውና ደህንነታቸው ተጠብቆ የተሻለ ሕይወት እንዲመሩ ከልብ በመነጨ ስሜት የተፀነሰ፣ ተፀንሶም ወደ ተግባር የተቀየረ ትልቅ ራዕይን የሰነቀ ስራ ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡
የእህቶችን ህይወት ለመቀየር፣ ለነገዋ የሴቶች የተሃድሶና ክህሎት ማበልፀጊያ ማዕከል በ2016 ዓ.ም ጀምረነው በ5 ዙር በተለያዩ የሙያ ዘርፎች 3 ሺህ 259 ሰልጣኞችን በክህሎት እና በስብዕና ግንባታ አሰልጥነን ወደ ስራ አሰማርተናልም ነው ያሉት፡፡
ሁሉም ተመራቂዎች ክብር ያለው ኑሮ፣ ብሩህ ተስፋን ሰንቀው አዲስ ህይወት መኖር እንደጀመሩም ከንቲባዋ አንስተዋል፡፡
“ከምንሰራቸው ስራዎች ሁሉ ትልቁ ስራ በሰው ላይ የምንሰራው፣ በተለይም በሴቶች ላይ የምንሰራው ነው” የሚለውን የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) መልዕክት የስራችን ማዕከል አድርገን እየፈፀምን እንገኛለን ብለዋል፡፡
በከተማችን ላይ ከሚታየው ለውጥ ሁሉ የሚልቀው በለነገዋ ሴቶች ላይ እያየን ያለው ለውጥ ነው ሲሉም ገልጸዋል፡፡
ለ”ለነገዋ የተሃድሶና ክህሎት ማበልፀጊያ ማዕከል” የሰነቅነው ራዕይ፣ በዓመት እስከ 10 ሺህ ሴቶችን የሚያበቃ፣ እንዲሁም አካታች ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጥ በኢትዮጵያ ብሎም በአፍሪካ ልምድ የሚቀሰምበት የልህቀት ማዕከል እንዲሆን ማስቻል ነው ብለዋል፡፡
ይህ ራዕይ በተሟላ ሁኔታ እንዲተገበር ሊደግፉን የመጡት የልጆች ኢንቨስትመንት ፈንድ ፋውንዴሽን (CIFF) መስራች ክሪስን በለነገዋ የሴቶች የተሃድሶና ክህሎት ማበልፀጊያ ማዕከል የምንሰራቸው ሰው ተኮር ስራዎች አስጎብኝተን በቀጣይም በጋራ በምንሰራቸው ስራዎች ዙሪያ ተወያይተናል ሲሉ ገልጸዋል፡፡
ከንቲባዋ አክለውም፤ ለራዕያችን ግብ ስኬት ሌት ተቀን ተግተን እንሰራለን፤ ፈጣሪም ይረዳናል ብለዋል፡፡