AMN – ነሐሴ 20/2018 ዓ.ም
አዲስ አበባን በክረምት ወራት ከሚከሰቱ የጎርፍ፣ የመሬት መንሸራተት እና የፍሳሽ ቱቦ መዘጋት አደጋዎች ለመከላከል መጠነ ሰፊ የንቅናቄ ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ።
የከተማዋ የጎርፍ አደጋ ተጋላጭነቶች እንደ መልክአ ምድራዊ አቀማመጥ፣ የመንገዶች አገነባብ ጉድለቶች፣ በወንዝ ዳርቻዎች የሚደረጉ ሕገወጥ ግንባታዎች፣ የፍሳሽ ማስወገጃዎች በአግባቡ አለመሰራት እንዲሁም ወንዞች በደለልና በቆሻሻ መደፈን ዋና ዋና ምክንያቶች መሆናቸው በጥናት ተለይቷል።
ይህን ስጋት ለመቅረፍ የአዲስ አበባ የእሳትና ድንገተኛ አደጋ ኮሚሽን ከከተማዋ መንገዶች ባለሥልጣን እና ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር ሰፊ የማስተካከያ ሥራዎችን አከናውኗል።
በወንዝ ዳርቻዎች ጎርፍ ወደ መኖሪያ አካባቢዎች እንዳይገባ የሚከላከሉ የድጋፍ ግንቦች እየተገነቡ ሲሆን፣ በደለልና በቆሻሻ የተደፈኑ የፍሳሽ ማስወገጃ ቱቦዎችን የማጽዳት፣ የመጠገን እና የማስፋፋት ሥራዎች ተጠናክረው ቀጥለዋል።
ከዚህ ባለፈም ነዋሪዎችን ያሳተፉ የአካባቢ ፅዳት ንቅናቄዎች በመካሄድ ላይ ይገኛሉ።
የአካባቢ ፅዳትና ውበት የመንግሥት ኃላፊነት ብቻ ሳይሆን የሁሉም ነዋሪ የጋራ ተግባር በመሆኑ፣ በንቅናቄው የተሳተፉት ነዋሪዎች የጎርፍ መውረጃ ቱቦዎችንና አካባቢያቸውን ከቆሻሻ በማፅዳት የዝናብ ውሃ ፍሰት እንዳይስተጓጎል አድርገዋል።
ይህ የነዋሪዎች ንቁ ተሳትፎ ንፁህ ፣ ውብና ለኑሮ ምቹ የሆነች ከተማን በጋራ ለመፍጠር ያለውን ቁርጠኝነት የሚያሳይ ነው።
የከተሞች ዘመናዊነትና ምቹነት ተፈጥሯዊ አደጋዎችን በሚቋቋሙበት አቅም የሚለካ በመሆኑ፣ ህብረተሰቡ አሁንም ቆሻሻዎችን በአግባቡ በማስወገድ እና የፍሳሽ ቱቦዎችን ከቆሻሻ ነፃ በማድረግ የየበኩሉን ኃላፊነት መወጣቱን ሊያጠናክር ይገባል።
በበረከት ጌታቸው