AMN- ነሐሴ 20/2018 ዓ.ም
አጣዳፊ የልብ ህመም ከምን ይመጣል? እንዴትስ መከላከል ይቻላል? የሚለውን የኸርት አታክ ኢትዮጵያ ዋና ሥራ አስኪያጅ እና የውስጥ ደዌ ሐኪም የሆኑት ዶክተር ኦብሴት መርዕድ ከኤ ኤም ኤን ጋር ባደረጉት ቆይታ አብራርተዋል፡፡
ዶክተር ኦብሴት እንደገለጹት፤ ለልብ ህመም አደጋ የሚያጋልጡ ዋና ዋና ምክንያቶች፤ ከፍተኛ የደም ግፊት፣ የስኳር ህመም እና የኮሌስትሮል መጨመር፣ ጤናማ ያልሆነ አመጋገብ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ እጥረት ናቸው፡፡
የልብ ህመምን አስቀድሞ መከላከል አነስተኛ ወጪ እንደሚጠይቅ በመግለጽ ሕመሙ ከተከሰተ በኋላ ግን ለሕክምና የሚወጣው ወጪ እጅግ ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ህመሙ ከተከሰተ በኋላ ጉዳቱን ሙሉ በሙሉ ወደ ነበረበት መመለስ አይቻልም የሚሉት ዶ/ር ኦብሴት መፍትሄዎች እና መወሰድ ያለባቸው እርምጃዎችንም አብራርተዋል፡፡
መፍትሄዎች እና መወሰድ ያለባቸው እርምጃዎች፡-
ሰዎች ሳይታመሙ የጤና ምርመራ ማድረግን መልመድ እንዳለባቸው ጠቅሰው ምርመራ የሚያስፈልገው ለመከላከል እንጂ ሁልጊዜ ለመታከም ብቻ አይደለም ሲሉ ገልጸዋል።
የአመጋገብ ሥርዓትን ማስተካከል፣ ጮማና ቅባት ያላቸውን ምግቦች መቀነስ፤ በአንጻሩ አትክልትና ፍራፍሬዎችን ማዘውተር ያስፈልጋል።
በተጨማሪም ስኳር፣ ነጭ ዳቦ፣ ሩዝ እና ፓስታን መቀነስ ከልክ በላይ ከሚመጣ ውፍረትና ከስኳር ሕመም ይታደጋል።
አዘውትሮ አካላዊ እንቅስቃሴ ማድረግ፣ በሳምንት ከ3 እስከ 4 ቀን፣ ቢያንስ ለ30 ደቂቃ ያህል የእግር ጉዞ ወይም ሌላ አካላዊ እንቅስቃሴ ማድረግ ለልብ ጤንነት እጅግ ወሳኝ መሆኑን ዶክተር ኦብሴት አስገንዝበዋል።
በፍሬሕይወት ብርሃኑ