AMN- ነሐሴ 19/2018 ዓ.ም
መጪውን የዘመን መለወጫ በዓል ተከትሎ ሰው ሰራሽ የምርት አቅርቦት እጥረት እንዳይከሰት በመዲናዋ የሚገኙ የሸማች ህብረት ስራ ማህበራት ዩኒየኖች አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት ማድረጋቸው ተገለጸ፡፡
የአዲስ አበባ ህብረት ስራ ኮሚሽን ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎች በዩኒየኖቹ በኩል እየተደረጉ ያሉ የዝግጅት ሥራዎችን አስመልክቶ በማህበራቱ የምርት መጋዘኖች ላይ ምልከታ አካሂደዋል፡፡
በምልከታቸውም፤ በዓሉን ታሳቢ ያደረጉ የግብርና እና የኢንዱስትሪ ምርቶች በበቂ መጠን መኖራቸውን ያረጋገጡ ሲሆን ህብረተሰቡ ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያገኝ የሚያስችሉ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑ ተገልጿል፡፡
የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር ሽታዬ መሃመድ እንዳስታወቁት፤ የሸማች ህብረት ሥራ ማህበራትን ከኢንዱስትሪ እና ከግብርና ምርት አምራቾች ጋር በቀጥታ በማስተሳሰር ከበዓላት የምርት አቅርቦት ባለፈ አስተማማኝ እና ዘላቂነት ያለው የገበያ ሰንሰለት እንዲኖር የሚያስችሉ ስራዎች ተከናውነዋል፡፡

መሰረታዊ የፍጆታ ምርቶች በማህበራቱ ሱቆችና መጋዘኖች በበቂ መጠን መግባት መጀመራቸውን በመግለጽ በቀጣይ ቀናትም ወደ መዲናዋ ምርቶችን በስፋት የማስገባቱ ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል፡፡
ማህበራቱ በመደበኛነት ከሚያቀርቧቸው ምርቶች በተጨማሪ በዓሉን ታሳቢ ያደረጉ አስፈላጊ የፍጆታ ምርቶችን በተለይም የግብርና፣ የኢንዱስትሪ እንዲሁም የእንስሳትና የእንስሳት ተዋጽኦ ምርቶችን በስፋት ለማቅረብ ዝግጅታቸውን አጠናቀዋል፡፡
የማህበራቱ አመራሮች በበኩላቸው፤ ኮሚሽኑ በፈጠረላቸው የገበያ ትስስር መሰረት ለበዓሉ አስፈላጊ የሆኑ ግብዓቶችን አዘጋጅተው ወደ መጋዘኖቻቸው ማስገባት መጀመራቸውን ተናግረዋል፡፡
ጤፍ እና የጥራጥሬ እህሎች፣ የምግብ ዘይት፣ ሽንኩርት፣ እንቁላል፣ ቅቤ እና ዱቄት እንዲሁም ሌሎች ምርቶች በመዲናዋ በሚገኙ የሸማች ህብረት ስራ ማህበራት መደበኛ ሱቆች፣ በሰንበት ገበያ፣ በበዓላት ባዛሮች እና ማህበራቱ ባዘመኗቸው ተቋማት በኩል ለሸማቹ እንደሚቀርቡ መገለጹን ከኮሚሽኑ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡