AMN- ጳጉሜን 2/2018 ዓ.ም
የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት እና ዋና ፅ/ቤት ኃላፊ አደም ፋራህ ከቱርክዬ አቻቸው፣ ከፍትህ እና ልማት ፓርቲ (ኤኬ ፓርቲ /AK Party) ምክትል ፕሬዚዳንት ዛፌር ሲራካያ ጋር የሁለትዮሽ ውይይት አካሂደዋል።
የሁለትዮሽ ውይይቱን ያካሄዱት በሴኡል ደቡብ ኮሪያ በመካሄድ ላይ በሚገኘው ዓለም አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲዎች (ICDPP) የምክክር መድረክ ጎን ለጎን ነው፡፡
ዘመናትን ያስቆጠረው የኢትዮ- ቱርክዬ የሕዝብ ለሕዝብ እና የመንግስት ለመንግስት ግንኙነት በንግድ፣ በኢንቨስትመንት በዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ተባብሮ ለመስራት እድሎችን የፈጠረ ነው፡፡
እነዚህን አጋጣሚዎች ይበልጥ አስፍቶ በፓርቲ ለፓርቲ ግንኙነት ማስቀጠል እንዲቻል በብልፅግና ፓርቲ እና በኤኬ ፓርቲ መካከል በጋራ ለመስራት ባሳለፍነው ዓመት በአዲስ አበባ የተፈረመው የሁለትዮሽ ስምምነት አጋዥ እንደሆነ በውይይቱ ተነስቷል።
በዋናነትም የጋራ ተጠቃሚነትን ለማስፋት የሁለትዮሽ ግንኙነትን በተለያዩ መስኮች አጠናክሮ በመቀጠል፣ የወጣቶች እና የሴቶች ክንፍን በጋራ የልምድ ልውውጥ መስኮች ተሳታፊ እንዲሆኑ በማድረግ እንዲሁም በአቅም ግንባታ መድረኮች የአመራሮችን አቅም በቀጣይነት እየገነቡ ለመሄድ የታቀዱ ስራዎች ወደ ተግባር ሊቀየሩ እንደሚገባ ተጠቅሷል።
በውይይቱ ላይ የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ፤ የፓርቲ ለፓርቲ ግንኙነትን ማጠናከር ለሀገራት ግንኙነት መጠናከር ያለው ፋይዳ ከፍተኛ በመሆኑ እንደ ብልፅግና ፓርቲ በቀጣይ በትኩረት የሚሰራበት መሆኑን ገልፀዋል።
እስከ አሁን የተደረሱ የሁለቱ ሀገራት ስምምነቶችን ከግብ ለማድረስ ቀጣይነት ያለው ጥረት እንደሚደረግ አንስተዋል።
ቱርክዬ በአዲስ አበባ ኤምባሲዋን የከፈተችበት እ.አ.አ በ2026 100ኛ ዓመት የሞላው ሲሆን በሁለቱ ፓርቲዎች መካከል ያለውን ግንኙነት የበለጠ ማጠናከር ለቀጣዩ ክፍለ ዘመን የጠበቀ ወዳጅነት ጠንካራ መሰረት የሚጥል መሆኑን መግለጻቸውን ከብልፅግና ፓርቲ ያገኘነው መረጃ ያሳያል።
አያይዘውም ይህንን ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስና ወደ ከፍተኛ ሀገራዊ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ እና ዲፕሎማሲያዊ ፋይዳ ለመቀየር ብልፅግና ፓርቲ በቁርጠኝነት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።