AMN- ግንቦት 6/2018 ዓ.ም
ከአንድ ምዕተ-አመት በፊት የተጀመረው የፈረንሳይና የኢትዮጵያ ወዳጅነት፤ ዛሬ በመሪዎች ቁርጠኝነት፣ በቴክኖሎጂ ሽግግር እና በስትራቴጂካዊ አጋርነት ታጅቦ አዲስ ምዕራፍ ላይ ይገኛል።
የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት በይፋ የተጀመረው እ.ኤ.አ በ1897 ፈረንሳይ በአዲስ አበባ ከተማ ኤምባሲዋን በከፈተችበ ወቅት እንደሆነ መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡
ይህ ግንኙነት በሊግ ኦፍ ኔሽንስ ወቅት ፈረንሳይ ለኢትዮጵያ ካሳየችው ድጋፍ ጀምሮ እስከ አሁኑ ዘመን ድረስ በፅኑ መሰረት ላይ ቆሞ ይገኛል፡፡
በተለይም የኢትዮ-ጅቡቲ የባቡር መስመር ግንባታ ለሁለቱ ሀገራት የንግድና የባህል ትስስር ዋነኛ መሰረት ጥሏል።
ይሁን እንጂ ባለፉት ስምንት ዓመታት ግንኙነቱ ከታሪካዊ ወዳጅነት ወደ ስትራቴጂካዊና ሁለገብ አጋርነት ተሸጋግሯል።
የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት አዲስ አቅጣጫ የያዘው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በጥቅምት 2011 ዓ.ም በፈረንሳይ ካደረጉት ጉብኝት ማግስት ነው።
ይህንን ተከትሎ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን እ.ኤ.አ በ2019 ወደ ኢትዮጵያ ያደረጉት ጉብኝት በሁለቱ ሀገራት መካከል የነበረውን ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ አሸጋግሮታል፡፡

በዚህ ጉብኝት ወቅት ማክሮን የገቡት ቃል ወደ ተግባር ተቀይሮ፣ የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት እድሳት መጀመር እና የኢዮቤልዩ ቤተ-መንግሥት እድሳት ውጤታማ በሆነ መልኩ ተከናውኗል።
ከቅርሶቹ ባሻገርም፣ ኢትዮጵያ የባህር ኃይሏን መልሳ ለማደራጀት ለምታደርገው ጥረት ፈረንሳይ የቴክኒክና የስልጠና ድጋፍ በማድረግ ላይ ትገኛለች።
በአሁኑ ወቅት የሁለቱ ሀገራት የኢኮኖሚ ትስስር ከ2.1 ቢሊየን ዶላር በላይ መድረሱ የትብብሩን ጥንካሬ ያሳያል፡፡
ከ60 በላይ የፈረንሳይ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ውስጥ በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ተሰማርተው እንደሚገኙ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት መረጃ ያሳያል፡፤
በተለይም የፈረንሳይ ባለሀብቶች በታዳሽ ኃይል፣ በአቪዬሽን፣ በመሠረተ ልማትና በግብርና ማቀነባበሪያ ዘርፎች ላይ ያላቸው ተሳትፎ እያደገ መጥቷል።
ሌላው የፈረንሳይ ልማት ኤጀንሲ በአዲስ አበባ እና በድሬዳዋ ዘላቂ የልማት ፕሮጀክቶችን በመተግበር ግንባር ቀደም ሚና እየተጫወተ ይገኛል።
ሰሞኑን በሁለቱ ሀገራት መሪዎች መካከል የተፈረሙት አዳዲስ ስምምነቶች የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ መሸጋገሩን ማሳያዎች ናቸው፡፡
በዚህም ፈረንሳይ ኢትዮጵያ ለጀመረችው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር እና ለታዳሽ ኃይል ልማት የገንዘብና የቴክኖሎጂ ድጋፏን ለማሳደግ ተስማምታለች።

ሌላው በኢትዮጵያ እየተተገበረ ያለውን የዲጂታል መታወቂያ እና የቴሌኮም ዘርፍ ነፃ ውድድርን ለመደገፍ ከፈረንሳይ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ጋር አብሮ ለመስራት ስምምነት ላይ ተደርሷል።
በፈረንሳይ መንግስት ድጋፍ የሚከናወኑ የግብርና ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ፓርኮችን በጋራ ማልማት፣ እንደ አዲስ የተደረገው የፊርማ ስምምነት መካከል ይገኝበታል፡፡
በተጨማሪም በምስራቅ አፍሪካ ያለውን የፀጥታ ሁኔታ ለማረጋጋት እና በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን ፈረንሳይ በስትራቴጂካዊ አጋርነት ለመቀጠል ቃል መግባቷም ተመላክቷል፡፡
እነዚህ አዳዲስ ስምምነቶች ኢትዮጵያ የጀመረችውን የኢኮኖሚ ሪፎርም በስኬት ለማጠናቀቅ ትልቅ አቅም እንደሚሆኑም ይጠበቃል።
የኢትዮጵያ እና የፈረንሳይ ግንኙነት ከታሪክ ማህደር ወጥቶ ወደ ተጨባጭ የልማት ሥራዎች እየተሸጋገረ ሲሆን፣ ይህ የጋራ ተጠቃሚነትን መርህ ያደረገው ወዳጅነት፣ በቀጣይ ዓመታት በንግድ፣ በቱሪዝም እና በቴክኖሎጂ ሽግግር ረገድ አዳዲስ ስኬቶችን እንደሚያስመዘግብ ይጠበቃል።
በአስማረ መኮንን