የቀይ ባህር ጉዳይ ለኢትዮጵያ የሉዓላዊነትና የህልውና ጉዳይ ነው

AMN- መስከረም 11/2019 ዓ.ም

የቀይ ባህር ጉዳይ ለኢትዮጵያ ከንግድና ገቢ ምንጭነት የዘለለ የሉዓላዊነትና የህልውና ጉዳይ መሆኑን መምህርና ተመራማሪ ተስፋዬ ጂማ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፌደራሊዝም እና ገቨርናንስ መምህርና ተመራማሪ ተስፋዬ ጂማ (ዶ/ር) እንደገለጹት፤ የባህር በር ማግኘት ሀገሪቱ የንግድ ልውውጧን ከማስፋፋት ባለፈ የግብርና እና የአሳ ሃብት ልማቷን ለማሳደግ ወሳኝ ሚና አለው፡፡

የቀይ ባህር ጉዳይ ለኢትዮጵያ ከንግድና ገቢ ምንጭነት የዘለለ የሉዓላዊነትና የህልውና ጉዳይ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

እንዲሁም ቀይ ባህር የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ምንጭ መሆኑን በመግለጽ ዲሎማሲያዊ ግንኙነትንም ለማጠናከር የባህር በር ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

የቀይ ባህር ተደራሽነት ለሀገሪቱ ሁለገብ ደህነትና ቀጣይ እድገት ዋስትና የሚሰጥ መሰረታዊ ጉዳይ መሆኑንም አንስተዋል።

ይሄንን በመረዳት የባህር በር ለማግኘት በትብብር መሥራት አለብንም ነው ያሉት መምህርና ተመራማሪው፡፡

የአዲስ አበባ አመራር አካዳሚ መሪ ተመራማሪ ሰለሞን ተፈራ በበኩላቸው፤የኢትዮጵያን የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄ በትክክል ለመረዳት የታሪክ፣ ሕጋዊና የጂኦፖለቲካዊ ዳራዎችን መመርመር ይገባል ብለዋል፡፡

እጅግ ተለዋዋጭ በሆነው የቀጣናው የጸጥታና ፖለቲካ ቁመና ውስጥ የባህር በር ባለቤት መሆን ለኢትዮጵያ የህልውናና የሉዓላዊነት ወሳኝ ጉዳይ መሆኑን አንስተዋል።

ምሁራን በጥናትና ምርምር የተደገፈ መረጃ በማመንጨት የሀገሪቱን ጥቅም በዓለም አቀፍ መድረኮች በማንሳትና በማስረዳት ለሀገራቸው ብሄራዊ ጥቅም መከበር አወንታዊ ሚና ማበርከት እንደሚችሉም ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያን የባህር በር ባለቤትነት ጉዳይ ምሁራን በአንድ ተቋም ተሰብሰበው በጥናትና ምርምር የፖሊሲ ሀሳቦችን በማመንጨት ጭምር በአጉራዊና ዓለም አቀፋዊ መድረኮች ሊያሰሙ ይገባል ያሉት ደግሞ፤የአባይና የቀይ ባህር ስትራቴጂክ ፎረም ሰብሳቢ አበበ ገመቹ (ዶ/ር) ናቸው፡፡

የአባይና የቀይ ባህር ስትራቴጂክ ፎረም ይህን አላማ ለማሳካት የተቋቋመ ስትራቴጂክ መድረክ መሆኑን በመግለጽ ከጂኦግራፊ፣ ከህዝብ ብዛት፣ ከፍትሃዊነትና ከቀጣናዊ ስትራቴጂክ አኳያ ጥናቶችን በማካሄድ የሀገሪቱን ጥቅም የሚያስከብሩ ሀሳቦችን እያመነጨ እንደሚገኝ አንስተዋል፡፡

የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄ ኢትዮጵያ በያዘችው የሰላማዊ ዲፕሎማሲያዊ መንገድ በማስቀጠል ተገቢና ፍትሃዊ የባህር በር ጥያቄዋን በጸኑ ማራመድ መቻሏም የሚደነቅ መሆኑን ገልጸዋል።

የባህር በር ባለቤት የነበረችው ኢትዮጵያ በሴራ ያጣችሁ የተፈጥሮ ሀብቷ አሁን ካለው የህዝብ ቁጥርና ፈጣን ኢኮኖሚ እድገቷ አኳያ የህልውና ጉዳይ ሆኗል።

ለዚህም የመደመር መንግስት የኢትዮጵያ ታሪካዊ፣ ተፈጥሯዊና ሕጋዊ የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄ በጠንካራ አቋም በማንጸባረቅ ላይ ይገኛል።

የሻምበል ምህረት

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review