ብርቱው ክንድ- የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት መከታ

You are currently viewing ብርቱው ክንድ- የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት መከታ
  • Post category:ፖለቲካ

AMN-መስከረም 13 /2019 ዓ.ም

ኢትዮጵያ ዘመናትን በተሻገረ የልጆቿ መስዋዕትነትና በፅኑ የመከላከል አቅሟ ሉዓላዊነቷን አስከብራና በነፃነቷ ተከብራ ኖራለች። ዛሬም የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የዚች ታላቅ ሀገር አለኝታ፣ የሰላሟ ዘብና የሉዓላዊነቷ ፅኑ መከታ በመሆን ግንባር ቀደሙን ስፍራ ይዞ ይገኛል።

ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ በስፋትና በጥልቀት የተካሄደው ተቋማዊ ሪፎርም በኢትዮጵያ የመከላከያ ታሪክ ውስጥ በልዩነት የሚጠቀስ ስኬቶችን አስመዝግቧል።

ቀደም ሲል የነበሩ ድክመቶችን በመቅረፍ፣ ሠራዊቱ የፓርቲና የቡድን ሳይሆን የሀገርና የህዝብ ብቸኛ አለኝታ እንዲሆን የተሰሩት ስራዎች ውጤት አስገኝተዋል። የተከናወነው የሪፎርም እርምጃ ሠራዊቱ በሙያዊ ብቃት፣ በገለልተኝነትና በጠንካራ ሀገራዊ ስሜት ላይ እንዲገነባ መሰረት ጥሏል።

በዘመናዊ የጦር አደረጃጀት፣ በሰው ኃይል ግንባታና በቴክኖሎጂ ሽግግር በኩል የተከናወኑት ተግባራት የመከላከያ ሠራዊትን አቅም አልቀው ብርቱ ክንድነቱን ማፅናት አስችለዋል።

ዛሬ የኢትዮጵያን ታላቅነት የሚመጥን ዘመናዊና የተሟላ የጦር መሣሪያ ትጥቅ፣ የዲጂታል ቴክኖሎጂ አጠቃቀም፣ የተራቀቁ ድሮኖችን ጨምሮ በሳይንስና በጥናት ላይ የተመሰረቱ የታላላቅ ወታደራዊ አቅሞች ባለቤት እንዲሆን ተደርጎ ሠራዊቱ ተገንብቷል።

የምድር ኃይል፣ የአየር ኃይል፣ የባህር ኃይልና የሳይበር ደህንነት ዘርፉ እርስ በርሳቸው በተቀናጀና በዘመናዊ አደረጃጀት በመጠናከራቸው የመከላከያ ሠራዊትን ስጋቶችን በብቃት የመመከት አቅም አልቆታል።

ከምንም በላይ የሰው ኃይሉ ወታደራዊ ስነ-ምግባር፣ ቁርጠኝነትና የሀገር ፍቅር የሠራዊቱ ትልቁ ጥንካሬው ነው። በከፍተኛ የውጊያና የቴክኖሎጂ ስልጠና የዳበረው ይህ ብርቱ ኃይል፣ ለማንኛውም አይነት የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ደንቃራዎችና ስጋቶች ለአፍታም ሸብረክ የማይል አቋም እንዳለው በተግባር አስመስክሯል።

የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ዛሬ ላይ የሀገራችንን ታላቅነት እና የነገ ብሩህ ተስፋዋን በሚመጥን ደረጃ ላይ ይገኛል።

ይህ ብርቱ ክንድ የኢትዮጵያን አንድነትና ህልውና ለማስጠበቅ፣ ሰላምና ልማቷን አስተማማኝ ለማድረግ ፈተናዎችን ሁሉ በብቃት ድባቅ የሚመታ፣ የኢትዮጵያ ኩራትና ሉዓላዊነት የማይበገር መከታ ሆኖ ይቀጥላል።

በታደሠ ሽፈራው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review