AMN – መስከረም 23/2019 ዓ.ም
በአዲስ አበባ ከተማ የተከበረው የኢሬቻ ሆራ ፊንፊኔ በዓል የመንግስት የስራ ኃላፊዎች፣ ልዩ ልዩ ብሔር ብሔረሰቦች፣ የውጭ ሀገር ዜጎችና ቱሪስቶች እንዲሁም በርካታ ታዳሚዎች በተገኙበት “ኢሬቻ ለብሔራዊ መግባባት ” በሚል መሪ ሀሳብ በደመቀና እሴቱን በጠበቀ መንገድ መከበሩን የአዲስ አበባ የተቀናጀ የፀጥታ ግብረ ኃይል አስታወቀ፡፡
በዓሉ ባህላዊ ይዘቱን ጠብቆ በድምቀትና ፍፁም ሠላማዊ በሆነ መንገድ እንዲከበር አባገዳዎች፣ ሀደ ሲንቄዎች፣ ፎሌዎች፣ የመዲናችን ነዋሪዎች እንዲሁም በየእርከኑ የሚገኙ የአስተዳደር አካላት ላደረጉት አስተዋፅኦ እና ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ለተወጡ የፀጥታና የደህንነት ተቋማት አመራሮችና አባላት የፀጥታ ግብረ ኃይሉ ምስጋናውን አቅርቧል፡፡

በነገው ዕለትም በቢሾፍቱ ከተማ የሚከበረው የሆረ አርሰዴ የኢሬቻ በዓል ባህላዊ ይዘቱን ጠብቆ እንዲከበር የፀጥታ ተቋማት ዝግጅታቸውን አጠናቀው ወደ ተግባር የገቡ ስለሆነ ህዝቡ የተለመደ ትብብሩን አጠናክሮ እንዲቀጥልም የአዲስ አበባ የተቀናጀ የጸጥታ ግብረ ኃይል ማስታወቁን ከአዲስ አበባ ፖሊስ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡