ከ30 ሺህ በላይ ልዑካን የሚታደሙበት ታላቅ አህጉራዊ የጤና ጉባኤ በአዲስ አበባ ይካሄዳል

You are currently viewing ከ30 ሺህ በላይ ልዑካን የሚታደሙበት ታላቅ አህጉራዊ የጤና ጉባኤ በአዲስ አበባ ይካሄዳል

AMN – ኅዳር 12/2019 ዓ.ም

ኢትዮጵያ 5ኛውን ዓለም አቀፍ የአፍሪካ የሕዝብ ጤና ጉባኤ (CPHIA 2026) ታስተናግዳለች። ጉባኤው በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል ከኅዳር 14 እስከ 18/2019 ዓ.ም ይከናወናል።

ከ100 በላይ ሀገራት የተውጣጡ ከ30 ሺህ በላይ ተሳታፊዎች በዚህ ታላቅ አህጉራዊ መድረክ ላይ እንደሚታደሙ ይጠበቃል።

በአፍሪካ የበሽታዎች መቆጣጠሪያ እና መከላከያ ማዕከል (Africa CDC) እና በኢትዮጵያ መንግሥት ትብብር የሚዘጋጀው ይህ ጉባኤ፤ “የአፍሪካ የጤና ደህንነት እና ሉዓላዊነት ከጤና ጥገኝነት እና ተጋላጭነት ወደ ባለቤትነት እና የማይበገር አቅም መሸጋገር” በሚል ዐቢይ መሪ ሀሳብ ይካሄዳል።

ይህ ዓመታዊ ጉባኤ የአፍሪካ የፖለቲካ መሪዎች፣ ፖሊሲ አውጪዎች፣ የሕዝብ ጤና ባለሙያዎች፣ ሳይንቲስቶች፣ የልማት አጋሮች፣ የግሉ ዘርፍ ተወካዮች እና የማኅበረሰብ አንቂዎች በአንድ መድረክ ተገናኝተው በአህጉሪቷ ቅድሚያ በሚሰጣቸው የጤና አጀንዳዎች የሚመክሩበት፣ ሳይንሳዊ ዕውቀቶችን የሚለዋወጡበት እንዲሁም አዳዲስ የፈጠራ መፍትሔዎችን የሚያስተዋውቁበት የትብብር ማዕቀፍ ነው።

በተጨማሪም ጉባኤው ትብብርን ለማጠናከር፣ ምርምርን ለማሳደግ እና የማይበገርና በራስ አቅም ላይ የተመረኮዘ የጤና ሥርዓት ለመገንባት የሚያስችሉ አፍሪካ-መር አካሄዶችን ለማጠናከር ሰፊ ዕድል ይፈጥራል።

እ.ኤ.አ. በታኅሣሥ 2021 በአፍሪካ ኅብረት (AU) እና በአፍሪካ ሲዲሲ (Africa CDC) ጥምረት በበይነ መረብ የተጀመረው ይህ ጉባኤ፣ ዛሬ ላይ በመላው አህጉሪቱ በሕዝብ ጤና ዙሪያ ለሚደረግ ውይይትና ትብብር ዋነኛ መድረክ ሆኖ እያገለገለ ይገኛል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጉባኤውን አስመልክተው ባስተላለፉት መልዕክት፣ ለአፍሪካዊያን እና ለዓለም አቀፍ የጉባኤው ተሳታፊዎች ወደ አዲስ አበባ እንኳን ደህና መጣችሁ ያሉ ሲሆን፣ ኢትዮጵያ ጉባኤውን ለማስተናገድ ሙሉ በሙሉ ዝግጁ መሆኗን አረጋግጠዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለውም፣ ይህ ጉባኤ የአፍሪካ ሀገራት ዕውቀታቸውን አንድ ላይ እንዲያሰባስቡ፣ አጋርነታቸውን እንዲያጠናክሩ እንዲሁም ጤናማ፣ የማይበገር እና በራስ አቅም ላይ የተመሠረተ መጻኢ ጊዜ ለመገንባት በሚያደርጉት ጥረት አፍሪካ-መር መፍትሔዎችን እንዲያራምዱ ወሳኝ ዕድል የሚሰጥ መሆኑን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ይህንን ታላቅ አህጉራዊ መድረክ በማስተናገዷ የተሰማትን ከፍተኛ ኩራት የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ከመላው አፍሪካ እና ከዓለም ዙሪያ የሚመጡ መሪዎችን፣ የኢኖቬሽን ባለሙያዎችን፣ ተመራማሪዎችን እና የልማት አጋሮችን ለመቀበል በከፍተኛ ጉጉት እንደምትጠባበቅ ማስታወቃቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review