ቃል በተግባር የታየባቸው 5 የስኬት ዓመታት!

AMN – መስከረም 25/2019

የኢ.ፌ.ዴ.ሪ መንግስት ላለፉት አምስት ዓመታት ያከናወናቸው ሀገራዊ የሪፎርም ስራዎች እና የተመዘገቡ ትልልቅ ውጤቶች ሰው ተኮር የሆኑ እና ለህዝብ ተጠቃሚነት ቅድሚያ የሰጡ ናቸው።

ኢትዮጵያ በነዚህ ዓመታት ውስጥ በርካታ ውስጣዊ እና ውጫዊ፣ ሰው ሰራሽ እና ተፈጥሯዊ ፈተናዎችን ብታስተናግድም፣ መንግስት የጀመራቸውን አገራዊ ለውጦች ከዳር ለማድረስ ባደረገው ጽኑ ጥረት ተጨባጭ ድሎችን ማስመዝገብ ችሏል።

ይህ ጊዜ ሀገሪቱ በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚ እና በማህበራዊ ዘርፎች የነበሩባትን መዋቅራዊ ማነቆዎች በመፍታት ወደ ብልፅግና የምታደርገውን ጉዞ በተግባር ያሳየችበት የታሪክ ምዕራፍ ነው።

ከታላላቅ ስኬቶች አንዱ በግብርናው ዘርፍ የታየው አስደናቂ የለውጥ እርምጃ ነው። መንግስት የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በወሰደው ቆራጥ አቋም፣ በተለይም የመኸር እና የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ኢትዮጵያን ከስንዴ ተቀባይነት ወደ ውጭ ላኪነት እንድትሸጋገር ትልቅ መሰረት ጥሏል።

ከዚህም ባሻገር፣ “የአረንጓዴ አሻራ” መርሃ ግብር በቢሊዮኖች የሚቆጠሩ ችግኞችን በመትከል የሀገሪቱን የደን ሽፋን ማሳደግ ብቻ ሳይሆን፣ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም፣ የከርሰ ምድር ውሃን ለማበልፀግ እና ሀገራዊ የቱሪዝም አቅምን ለማሳደግ የሚያስችል ዓለም አቀፋዊ አርዓያነት ያለው ስራ በተግባር ተከናውኗል።

በሌላ በኩል፣ ሀገራዊ የሜጋ ፕሮጀክቶች ግንባታ ቃልን ወደ ተግባር የመቀየር ሌላው ግዙፍ ማሳያ ነው። የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ዲፕሎማሲያዊ እና ፋይናንሳዊ ፈተናዎችን ሁሉ ተቋቁሞ የውሃ ሙሌት እና የኃይል ማመንጨት ምዕራፍ ላይ መድረሱ የኢትዮጵያውያንን የዘመናት ህልም እውን ያደረገ ነው።

በተጨማሪም፣ በገበታ ለሸገር፣ ገበታ ለሀገር እና ገበታ ለትውልድ ፕሮጀክቶች የተገነቡት ፓርኮች፣ የሳይንስ ሙዚየም፣ የዓድዋ ድል መታሰቢያ፣ አብርሆት ቤተ-መጽሐፍት፣ እንዲሁም የከተሞች ኮሪደር ልማት ስራዎች የሀገሪቱን ገፅታ ከመቀየር ባለፈ ለቱሪዝም እና ለስራ ዕድል ፈጠራ ትልቅ አስተዋፅዖ አበርክተዋል።

የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ (Homegrown Economic Reform) ትግበራም የነዚህ አምስት ዓመታት ትልቅ የሪፎርም አካል ሆኖ ተመዝግቧል። ይህ ማሻሻያ የፋይናንስ ዘርፉን ክፍት በማድረግ እና የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን በመሳብ የኢኮኖሚውን መዋቅራዊ ችግሮች ለመፍታት አስችሏል።

በተጓዳኝም “ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025” ስትራቴጂን በመተግበር የቴሌኮም ዘርፉን ነፃ ማድረግ፣ የቴክኖሎጂ መሰረተ ልማቶችን ማስፋፋት፣ የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮጀክትን መጀመር እና የመንግስት አገልግሎቶችን በማዘመን የዜጎችን እንግልት የሚቀንሱ ዘመናዊ አሰራሮች ተዘርግተዋል።

በመንግስት እና በተቋማት ግንባታ ረገድ የተሰሩት ስራዎችም የሀገሪቱን ሉዓላዊነት እና ሰላም ለማስጠበቅ ወሳኝ ሚና ተጫውተዋል። ምንም እንኳን ሀገሪቱ በሰሜኑ ክፍል የገጠማት ጦርነት እና አለመረጋጋት ከባድ ቢሆንም፣ በፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ችግሮችን በውይይት መፍታት መቻሉ የመንግስትን የሰላም ቁርጠኝነት አሳይቷል።

ከዚህም ጋር ተያይዞ የፀጥታ፣ የፍትህ እና የዴሞክራሲ ተቋማትን ከፖለቲካዊ ወገንተኝነት ነፃ በማድረግ የህዝብ አመኔታን ለመገንባት እና የብሔራዊ መግባባት ኮሚሽንን በማቋቋም ዘላቂ ሰላም ለማምጣት የተጀመሩት የሪፎርም ስራዎች የዚሁ ስኬት አካል ናቸው።

ባለፉት አምስት ዓመታት የኢ.ፌ.ዴ.ሪ መንግስት “ቃል በተግባር” በሚል መርህ የተጓዘበት መንገድ ኢትዮጵያ ጠንካራ እና የበለፀገች ሀገር እንድትሆን የሚያስችል ፅኑ መሰረት የጣለ ነው።

የተከናወኑት ግዙፍ ፕሮጀክቶች፣ የተተገበሩት የኢኮኖሚ፣ የዲጂታል እና የፖለቲካ ሪፎርሞች፣ እንዲሁም በግብርናው ዘርፍ የተመዘገቡት ድሎች ሀገሪቱ ያላትን እምቅ አቅም በተግባር ያሳዩ ናቸው።

ይህንኑ የለውጥ እና የስኬት ጉዞ ማስቀጠል የሚያስችላትን 7ኛውን ጠቅላላ ምርጫ በስኬት ያከናወነችው ኢትዮጵያ፣ ለቀጣዮቹ አምስት አመታት የሚመራትን መንግስት በዛሬው ዕለት በመመስረት ላይ ትገኛለች።

ይህ አዲስ መንግስት የጀመራቸውን ስራዎች ይበልጥ አጠናክሮ በመቀጠል እና ያሉትን ተግዳሮቶች በጋራ በማለፍ፣ የዜጎችን የኑሮ ደረጃ በማሻሻል ኢትዮጵያን ወደ ተሻለ የብልፅግና ከፍታ እንደሚያሸጋግራት ፅኑ ተስፋ ተጥሎበታል።

በሹመት ደመቀ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review